Breaking News
Home / Amharic / “ፍርድ ቤቱ የፈፀመብን በደል!”

“ፍርድ ቤቱ የፈፀመብን በደል!”

“ፍርድ ቤቱ የፈፀመብን በደል!”

እነክርስቲያን ታደለ ከቂሊንጦ ማረሚያ ቤት፤
***
እኛ በፖለቲካ አመለካከታችን ብቻ በመንግሥት የፈጠራ ክስ ተደርሶልን በአስር አለቃ መሳፍንት ጥጋቡ መዝገብ ስር ተከሰን ላለፉት 7 ወራት በሕገወጥ እስር ላይ የምንገኝ የአብን አባላትና አመራሮች ላይ ጉዳያችንን በማየት ላይ የሚገኙት የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በርካታ በደሎችን ፈፅሞብናል። ለአብነትም፦

1. ተከሳሾች ካቀረብነው መቃወሚያ ውጭ ብይን መስጠታቸው፦
ተከሳሾች በ.ተ.ቁ 13 ስር አቃቤ ህግ ከዘረዘራቸው የሰነድ እና ሌሎች ማስረጃወች ውስጥ ለተከሳሾች የማይደርሱ በማለት የዘረዘራቸው ማስረጃወች ሊደርሱን ይገባል፤ ይህ ከህግ ውጭ ነው። አቃቤ ሕግ ለፍርድ ቤት ብቻ ለይቶ ለተከሳሺ ሳያደርስ የሚያቀርበው ማስረጃ ሊኖር አይገባም፤ ይህ ካልሆነ ግን ለመከራከር እና ማስረጃ ለማቅረብ አያመቸንም፤ ሥለዚህ ለእኛ ለተከሳሾችም ደርሶን ማስረጃውን እና ክሱን በማየት ልንከራከር ይገባል። ስለሆነም በማስረጃ ዝርዝር ተ.ቁ 5 ስር በ 2ኛ ተከሳሽ( አስጠራው ከበደ)፣ 12ኛ ተከሳሽ( ክርስቲያን ታደለ) እና 9ኛ ተከሳሽ( አየለ አስማረ) ተከሳሾች፣ በማስረጃ ዝርዝር ተ.ቁ 19 ስር በ 2ኛ ተከሳሺ( አስጠራው ከበደ)፣ በማስረጃ ዝርዝር ተ.ቁ 21 ስር በ 3ኛ ተከሳሺ ( ሲሳይ አልታሰብ) ላይ የቀረቡት ማስረጃወች እንዲደርሱን እንዲታዘዝልን በማለት መቃወሚያ አቅርበን እያለ ፍ/ቤቱ ግን ካቀረብነው መቃወሚያ ውጭ ስለ ምስክሮች ስም መዘርዘር አለመዘርዘር ሕጋዊነት ብይን የሰጠ ሲሆን ይሄም ሙሉ በሙሉ እኛ ከጠየቅነው ውጭ ብይን በመስጠት ሆን ብሎ አልፎታል። ከዚያም በኃላ ድጋሚ ጠይቀን ዝም ብሎ አልፎ በዚህ ሁኔታ የእምነት ቃል እንድንሰጥ አስገድዶናል። ይህም የፓለቲካ እጅ ያለበት ክስ ድርሰት ተጠቃሎ አለማለቁን የሚያሳይ ነው።

2. 9ኛ ተከሳሺን በ21/4/2012 ከነበረው ቀጠሮ በሓላ ለብቻ በችሎት ቀርቦ የተዛተበት መሆኑ፦
9ኛ ተከሳሺ የሆነው አየለ አስማረ ለብቻው በዚሁ ቀን በችሎት እንዲቀርብ በማድረግ በ21/4/2012 ዓ.ም በነበረው ቀጠሮ ስትወጣ ለደጋፊዎች እጅህን አውጥተህ መፈክር በማሰማት ችሎት ደፍረኃል በሚል ጠበቆች በሌሉበት ማስጠንቀቂያ የሰጡት እና ችሎቱ በቀጣይ እርምጃ ይወስድብኃል በማለት የተዛተበት መሆኑ።

3. ጠበቆቻችን በነጻነት እንዳይከራከሩ ማስጠንቀቂያ መስጠታቸው፦
የሙያ አገልግሎት እየሰጡን ከሚገኙ ጠበቆች ውስጥ አንዱ የሆነውን ጠበቃ ሔኖክ አክሊሉን በ21/4/2012 በነበረው ቀጠሮ ችሎቱ እስኪጠናቀቅ ቆይቶ በአግባቡ ከችሎት ከወጣ በኃላ በቀጣይ ቀጠሮ የችሎት ቀን ግን ጠበቃው በስራ መደራረብ ችሎት ባይቀርብም ባለፈው ቀጠሮ ለተከሳሾች መኪና ውስጥ ከገቡ በኃላ ችሎት ተረብሾ ዳኞች አቋርጠን ቢሮ ከገባን በኃላ እጁን አውጥቶ “አስገባህለት’’ የሚል የሚመስል ምልክት አሳይቷል በማለት ማን እንዳየው ሳይዘረዝሩ፣ የቀረበበትን ማስረጃ ሳይገልጹ፣ የእርሱን ኃሳብ ሳይሰሙ ትእዛዝ ሰጥተናል ብለው በመቅረብ ማስጠንቀቂያ በሌለበት መሰጠቱ።

4. ሊዘግቡ የመጡ የሚዲያ አካላትን ጋዜጠኞችን ችሎቱ ጉዳያችንን በነፃነት እንዳይዘግቡ ማስፈራራቱ፦
ጉዳያችን ሊከታተሉና ሊዘግቡ የመጡ ጋዜጠኞችን ለማስፈራራት ስም ጻፉ የተባሉ እና ችሎቱ ሳያብራራ የተዛባ መረጃ የምታቀርቡ አላችሁ ወደፊት ይጣራል በማለት እርምጃ እንደሚወስድ ገልጾ ያስፈራራቸው እና ወደፊት ፈርተው ቀርበው ጉዳያችንን እንዳይዘግቡ ጫና የፈጠረባቸው መሆኑ።

5. ተከሳሾች በሌለንበት ወደ ፍርድ ቤት የሚገባ ሰው ይቀነስ ብሎ ትእዛዝ ሰጥቶ ደጋፊዎቻችን አሳስሮ ያስደበደበብን መሆኑ፦
ተከሳሾች በሌለንበት ከፍ/ቤት አሰራር ውጭ ችሎት አየተረበሸ ነው በሚል ደጋፊዎቻችን፣ ቤተሰቦቻችንና ሌሎች የሕብረተሰብ ክፍሎች በግልጽ ችሎት የሚደረግን ክርክር እንዳይታደሙ በማድረግ እና እንዴት እንደሚመፈጸም ባልተብራራ ሁኔታ በቀጣይ ችሎት የሚመጣ ሰው እንዲቀነስ በሌለንበት ቀደም ብሎ ትእዛዝ በመስጠቱ የልብ ልብ የተሰማው ፓሊስ ከፍ/ቤት መቶ ሜትር ራዲየስ በሁሉም አቅጣጫ በመክበብ የተከሳሾችን ጉዳይ ሊከታተል የመጣውን ህዝብ፤ ቤተሰብ፣ ጋዜጠኞች እና ብሔራቸው እየተጠየቀ “አማራ” የሆኑትን እየለየ እየተደበደቡ በጅምላ እንዲታሰሩ አስደርጎብናል። አካል ጉዳተኞችና እድሜያቸው 18 ያልሞላ ተማሪዎች ሳይቀር ለሌላ ስራ በአካባቢው በመንገድ ላይ ሲንቀሳቀሱ ማንነታቸውን ተጠይቀው “አማራ” ስለሆኑ ብቻ እየተደበደቡ በጂምላ ታስረዋል። በዚህም በተጨማሪ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ደጋፊዎቻችን ማረሚያ ቤት በመገኘት ተሰልፈው ገብተው እየጠየቁን በቃ ሲባል በሰላም እየተመለሱ እያለ በችሎት ወጥተን ወደመኪና ስንገባ እና ስንወርድ ብቻ ድጋፍ ለመስጠት ከዚህ በፊት በግዜ ቀጠሮ እንደነበረው ችሎት፣ እዚህም ችሎት ለአጭር ደቂቃ ተቃውሞ አሰምተው በሰላም ተበትነው እያለ ችሎቱ መከልከሉ የሚያሳዝንና ከጀርባው የፖለቲካ ውሳኔ ያለበት መሆኑን በግልፅ ያሳየ ነው። ይህ ሁሉ በደል የደረሰው ችሎቱ ከአስፈጻሚው ጋር ተነጋግሮ በሰጠው ትእዛዝ ምክንያት ነው። ማንነታቸው እየተለየ አማራ በመሆናቸው ብቻ የተደበደቡት እና የታሰሩት አማራዎች ደም በችሎቱ እጂ ነው።

6. ከሕግ ውጭ ቀጣይ የፍርድ ሂደቱ ችሎት በፕላዝማ ይሁን መባሉ፦
ችሎቱ በሌለንበት ትእዛዝ ሰጥቶ ከላይ ያቀረብነው በደል ደርሶብን እያለ ሁኔታውን አይተን ከመጣንበት መኪና ተከሳሾች አንወርድም ብለን እያለ ገብቶ በመሰየም ብንቀርብም ባንቀርብም የማይቀየር ከዚህ በኃላ ያለው ችሎት በፕላዝማ ይደረግ የሚል ገለልተኛ አለመሆኑን ያጋለጠ ውሳኔ ሰጥቷል። እውነት ተሸፍፍኖ እንዳይወጣ በመንግስት በኩል የሚካሔደውን የሰኔ 15ን የወንድሞቻችንን ግድያ ፓለቲካዊ ተንኮል በማገዝ፣ በጠበቆቻችን ጋር በማንገናኝበት መልኩ፣ ሌላው ቢቀር የሟች ቤተሰቦችን የሐሰት ድሪቶ ክስ እንዳይከታተሉ ለማድረግ በማሰብ በተልካሻ ምክንያቶች በፕላዝማ ቃል እንድንሰጥ ይደረግ በማለት የሰጠው ትእዛዝ ታሪክ የሚመዘግበው አሳፋሪ ውሳኔ ነው።

በአጠቃላይ ከላይ በቀረበው ምክንያት ችሎት የሚመጣው ሰው አንድም ሰው ሆነ ሃምሳ ሺ ያለምንም ገደብ በችሎት ግቢ ተገኝቶ በግልጽ ችሎት የሚደረግ ካልሆነ እንዲሁም አቃቤ ህግ ለተከሳሽ የማይደርሱ ለፍርድ ቤት ብቻ የሚቀርቡ ብሎ የዘረዘራቸው የክስ ማስረጃዎች ለእኛ ባላደረሰበት ሁኔታ ተጠቃሎ ያላለቀና ለእኛም ያልቀረበ ክስና የክስ ማስረጃ ባለበት ሁኔታ በፕላዝማ ቀርበን ቃል የማንሰጥና የማንከታተል መሆኑ ታውቆ ችልቱ የመሰለውን ፍርድ በሌለንበት ከአቃቤ ሕግ ጋር እንዲሰጥ እንጠይቃለን። ከዚህ ታልፎ ከታሰርንበት ማረፊያ ቤት በጉልበት በማረሚያ ቤቱ ፓሊስ ተገደን በፕላዝማ ቃል እንድንሰጥ ችሎቱ በፍ/ቤቱ የታሰበው አደገኛ አካሔድ ምክንያት ለሚደርስብን ማናቸውም ጉዳት ኃላፊነት ከመንግስት ጋር በመተባበር ትእዛዝ የሰጠው ችሎት እንደሆነ መላ የአማራ ሕዝብና ፍትኅን ናፋቂ ኢትዮጵያውያን ዘንድ እንዲታወቅልን እንፈልጋለን።

መላ ሕዝባችንም ይህንን እውነት ተገንዝቦ እኛ ለእውነተኛ ፍትህ የቱንም ዋጋ ለመክፈል ዝግጁ መሆናችንን በመገንዘብ ለፍትህ መስፈን እንዲሁም ለአማራው ሁለንተናዊ ነፃነት ይታገል ዘንድ እየሄድንበት ያለው መንገድ አንቂ ደወል ሊሆነውና በተቀናጀ ክንድ ሊታገል ይገባዋል።

ዝንተ-ዓለም አማራ!

Check Also

ሰሎሞን ካሳ ማነው? Who is Solomon Kassa?

አንከር ሚዲያ እንደዘገበው .. ለማታውቁት ሰለሞን ካሳ ይባላል ., ወንጀለኛው የሆነው ይህ ሰው የህዝብ ድምፅ …

የአድዋ በአል በለንደን ከተማ በደማቅ ተከበረ

Multi threaded Redundant Dedicated Server in USA and in Europe.