Breaking News
Home / News / የዘውግ ፖለቲካና ዘር ማፅዳት::

የዘውግ ፖለቲካና ዘር ማፅዳት::

ዶ/ር ሰማኸኝ ጋሹ

የዘር ማፅዳት ወንጀል በዓለማችን ታሪክ የነበረ ነገር ቢሆንም በተለይ ከቀድሞዋ ዩጎዝላቪያ መበተን ጋር ተያይዞ በተፈፀሙት ወንጀሎች ትኩረት ያገኘ በሕዝብ ላይ የሚፈፀም የማሳደድድና የማፈናቀል ወንጀል ነው። እኤአ ከ1992-1995 በተካሄደው የቦስንያ ሄርዞጎቪና ጦርነት ሙስሊሞችና ክሩአቶችን ሰርቦች በግዳጅ ቀያቸዉን እንዲለቁ በማድረጋቸው ከአንድ መቶ ሺሕ በላይ ሙስሊሞችና ክሮአቶች የዘር ማፅዳት ወንጀል ሰለባ ሆነዋል።

በቅርቡም በባንግላዴሽ የሚኖሩት ሦስት መቶ ሺሕ የሮሄንጊያ ማኅበረሰብ አባላት በገፍ ከቀያቸዉ እንዲሰደዱ የተደረገበትን ዓለምን ያሳዘነ ድርጊት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የዘር ማፅዳት ወንጀል በሚል ኮንኖታል። የተባባሩት መንግሥታትት ድርጅት የኤክስፐርቶች ኮምሽን የዘር ማፅዳት ወንጀልን “a purposeful policy designed by one ethnic or religious group to remove by violent and terror-inspiring means the civilian population of another ethnic or religious group from certain geographic areas” (ሆነ ተብሎ በተቀረፀ ፖሊሲ አንድ ዘውግ ወይም የሃይማኖት ቡድን ሲቪል ሕዝብን ወይም ሌላ ዘዉግን ወይም የሃይማኖት አባላትን በሃይል ወይም በማስፈራራት ከአንድ አካባቢ እንዲለቁ ማድረግ ነዉ።) የዘር ማፅዳት ወንጀል ዋና አላማ አንድ ቡድን የእኔ ብቻ ነው ከሚለዉ አካባቢ የሌላ ዘዉግ አባላትትን በማስወጣት አንድ ወጥ (homogenous) ማኅበረሰብ ለመፍጠር ነዉ። የዘር ማፅዳት ወንጀል በብዛት የሚፈፀመው በአብዛኛዉ ዘውጋዊ ስሜቶች በገነኑበትና የፖለቲካ መሣርያ ሆነው በሚያገለገሉበት የዓለማችን አካባቢዎች ነው።

በአገራችን ሰሞኑን በለገጣፎ አካባቢ ብሔርን መሰረት አድርጎ የተፈፀመው መፈናቀል የህዝብን ትኩረት የሳበ አሳዛኝ ክስተት ሆኖ አልፏል። ከዚህም በተጨማሪ በበርካታ ኢትዮጵያዉያን ዘንድ ለኢትዮጵያዊነት ፍቅር አንገታቸዉን ይሰጣሉ የተባሉት አቶ ለማ መገርሳ ከሶማሌ ክልል የተፈናቀሉ የኦሮሞ ተወላጆችን ወደ ቀያቸው ከመመለስ ይልቅ በአዲስ አበባና በዙርያዋ አካባቢ እንዲሰፍሩ በማድረግ የእኔ የሚሉትን ሕዝብ ከተሞችን እንዲቆጣጠር እየሰሩ እንደሆነ ገልፀዋል። ከዚህም በተጨማሪ ፊንፊኔ ኬኛ በሚባለዉ የስግብግብነት ፖለቲካ በሕገወጥ መንገድ ለአንድ አካባቢ ሰዎች መታወቂያ እየተሰጠ እንደሆነ ማስረጃዎች ወጥተዋል። ይህን አይነት ዐይን ያወጣ አድልዎና የዴሞግራፊክ ምህንድስና አሠራር ህዝብን ያሳዘነዉ ቲም ለማ የሚባለዉ ቡድን ይምልና ይገዘትበት ከነበረዉና ሕዝቡ ድጋፉን እንዲሰጠዉ ካደረገዉ ‘የኢትዮጵያዊነት’ ትርክት በተቃራኒ የቆመ መሆኑ ነዉ።

ሕወሓት ያደርገዉ የነበረዉ የዘረኝነት አካሄድ አሁንም መልኩን ቀይሮ በመካሄድ ላይ እንዳለ በቂ ምልክቶች እየታዩ ነዉ። ይህን ዓይነት አካሄድም በኬኛ ፖለቲካ ታጅቦ በተጠናከረ መልኩ እንደሚቀጥል ለማወቅ ነብይ መሆን አይጠይቅም። ምናልባት ኢትዮጵያ የምትባለዉ አገር ታሪክ ከመሆንዋ በፊት ከዚህ አገር ከሚያፈርስ መርዘኛ የዘረኝነት አካሄድ ለመዉጣት የበሽታዉን ምልክቶች ሳይሆን የበሽታዉን ስርና መሰረት ማወቅና ማከም ያስፈልጋል።

ወደድንም ጠላን ለዘር ማፅዳት ወንጀል የዳረገን ሰሞኑን እነ ዶ/ር አብይ አንደራደርበትም ያሉት የዘዉግ ፌዴራሊዝም መሆኑን መገንዘቡ በጣም አስፈላጊ ነዉ። ስራ ላይ ያለዉ ህገ መንግስት የማእዘን እራስ የሆነዉ ‘የብሄሮችን የራስን እድል በራስ የመወሰን እስከ መገንጠል’ ርእዮተ አለም ታሪካዊ አመጣጡ፣ ትርጉሙና በእኛም ሆነ በሌሎች አገሮች ተግባራዊ የሆነበት መንገድ ከዴሞግራፊ ምህንድስናና ዘር ማፅዳት ጋር የቅርብ ትስስር ያለዉ ነዉ። በኢትዮጵያ የግራ ፖለቲካን ያራመዱት ኅይሎች የተከተሉት ‘የብሃር ጭቆና’ ትርክት በሩስያ ከተካሄደዉ የሶሻሊስት አብዮት ጋር የቅርብ ትስስር ያለዉ ነዉ። ሌኒንና ስታሊን በሩስያ አብዮት ለማካሄድ ዝግጅት ሲያደርጉ ሩስያዊ ካልሆኑት ልሂቃን የሚነሳዉን የዘዉግ ጥያቅ ለመመለስ ሲሉ በብሔር ጉዳይ ላይ ያተኮረ ‘ ማርክሲዝምና የብሄር ጥያቄ’ የሚል ጽሑፍ አወጡ። ስታሊን ለብሄር የሰጠዉ ትርጉም አሁን በእኛ ሕገ መንግሥት የተካተትዉን ትርጉም የያዘ ሲሆን ለብሔር ጥያቅ መፍትሔውም ‘ የራስን እድል በራስ መወሰን እስከ መገንጠል’ ነው ተብሎ ተቀመጠ። ከ1924 ጀምሮ በነበሩት ሕገ መንግሥቶች በሙሉ ይህ መርህ የሕገ መንግሥታቸው ዋና አካል ሆኖ ቀጠለ።

በአገራችን በየአካባቢዉ እየተካሄደ ያለዉን የዘር ማፅዳት ለመረዳት በሶቭየት ኅብረት የነበረዉን ሁኔታ መረዳት በጣም ይጠቅማል። ሶቭየት ኅብረት የራስን እድል በራስ መወሰን እስከመገንጠል የተባለዉን የስታሊን ሃሳብ ተግባራዊ ካደረጉ በሁዋላ ሌሎች ብሔሮች በሩስያ ጭቆና ዉስጥ ነበሩ በሚል ሁሉም ብሔሮች የኔ ነዉ የሚሉት ክልል እንዲኖራቸዉ ተደረገ። እያንዳንዱ ብሔር የራሱ ባንዲራ፣ መንግሥትና መሬት እንዲኖረው ተደረገ።

በየካባቢዉ ይኖሩ የነበሩ የሌላ ብሔር ተወላጆች በባቡር እየተጫኑ ወደ እናት ክልላቸዉ በገፍ እንዲመለሱ ተደረገ። እነ ስታሊን ሕዝቡ አገራዊ አመለካከት እንዲኖረዉ የማይፈልጉ የነበረ ሲሆን እንደዉም ማንኛዉም ሰዉ በተቻለ መጠን አገራዊ ማንነት እንዳይኖረውና አካባቢያዊ ማንነቱን እንዲያዳብር ያበረታቱ ነበር። በ1920ዎቹና 30ዎቹ ስታሊን በወሰደዉ የዘር ማጥራት ፕሮጀክት ራሳቸዉን እንደ አንድ ብሄር የማያዩ የነበሩትን ማህበረሰቦች መቀየር አስቸጋሪ እየሆነ ሲመጣ ሰዎች በግዳጅ አንድ ብሄር እንዲመርጡ ማስገደድ ተደረገ። ይህ የስታሊን ፕሮጀክት በተለያዩ ማኅበረሰቦች መካከል የነበረዉን ሰላማዊ ግንኙነት ሙሉ በሙሉ ወደ ተቀናቃኝነትና ጠላትነት ቀየረዉ። ማህበረሰቦች የጎሪጥ መተያየት ጀመሩ። በአንድ መልኩ ልዩነትን እያበረታቱ በሌላ በኩል ደግሞ ኮሚኒስት ፓርቲዉ ሁሉንም ሥልጣን መቆጣጠሩን መቀጠሉ የፈጠረዉ ቅራኔ አገሪቱን ሊበትናት ችሎአል።

ወደ ሀገራችን ስንመለስ ያላዋቂ ሳሚ የሆኑት ጥራዝ ነጠቆቹ የ 1960ዎቹ የተማሪዎች እንቅስቃሴ መሪዎች አገራቸዉንም ሆነ ማርክሲዝምን በቅጡ ሳይረዱ የስታሊንን የብሄር ጭቆና ትርክት እንዳለ በመኮረጅ አማራን በጨቋኝነት ሌላዉን በተጨቋኝነት በመፈረጅ አገሪቱን ቀዉስ የከተተዉን መርዝ በአገሪቱ ፖለቲካዉ ዉስጥ ተከሉ። የዚህ የተማሪዎች እንቅስቃሴ ዉላጅ የሆነዉና በአማራዉ ጥላቻ ያበደዉ ህወሃት ስልጣን ላይ ሲወጣ ከላይ የተገለፀዉን የስታሊንን መርህ በሕገ መንግሥት በማስፈር ተመሳሳይ ዘር የማፅዳት ስራ አካሄደ። ሕዝቡን በጎሳ ክልል በማጠር ኢትዮጵያዊነትን ወንጀል በማድረግ ህዝቡ በሙሉ በግድ ጎሳ እንዲኖረዉ አደረገ። ይህ ሰይጣናዊ ተልእኮ ላለፉት 27 አመታት ያመጣዉን ቀዉስ ለመግለፅ አስቸጋሪ ነዉ።

ከዐሥር ወራት በፊት ወደ ሥልጣን የመጡት ጠ/ሚኒስትር ዐቢይ ከተሾሙበት ቀን ጀምሮ ስለ ኢትዮጵያዊነት የሚያደርጉት ዲስኩር ሕዝብን አይደለም ወፍን ከሰማይ ማዉረድ የሚችል ነበር። ህዝቡ ከዚህ የዘረኝነት ስርአት የተላቀቀ መስሎት ከዳር እስከ ዳር ድጋፉን ሰጣቸዉ። ከአርባ አመታት በላይ ፖለቲካ ዉስጥ ነበርን የሚሉት የተቃዋሚ መሪዎችም የለዉጡ አቅጣጫና ፍኖተ ካርታ ምንድነዉ ብለዉ ሳይጠይቁ ለዉጡ እንዳይደናቀፍ በሚል አብረዉ መነዳት ጀመሩ። ዶሮ ብታልም ጥሬዋን እንደሚባለዉ በኢትዮጵያ ሱሴነት የሚታወቀዉ የቲም ለማ ቡድን በአፍ ከሚገለፀው ኢትዮጵያዊነት ዉጭ መሰረታዉ የፖሊስ ለዉጥ ካለማድረጋቸውም በላይ በጎሳ ፌዴራሊዝም እንደማይደራደሩ፥ በአዲስ አበባ ላይ ያላቸዉን ልዩ መብትና አፋን ኦሮሞን ብሔራዊ ቋንቋ የማድረጉን ሥራ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ግልፅ አደረጉ። ከዚህም ባላፈ እነዚህ ሰዎች ላለፉት 27 ዓመታት ከተሰነቀሩበት የጎሰኝነት ዋሻ ስለመውጣታቸዉ ብዙ ማስረጃ ማቅረብ አልተቻለም።

እንዲያም ባለፉት ወራቶች የተፈፀሙትን ድርጊቶች ስንመረምር ለውጡ በዋናነት ከህወሃት ወደ ኦዴፓ ሥልጣን የመሸጋሸግ ጉዳይ እንደሆነ መረዳት ይቻላል። እነ ኢትዮጵያ ሱሴዎች ለቡራዩ የዘር ማፅዳት ያሳዩት ወገንተኘነት፥ የአዲስ አበባን ሕዝብ አፍሰዉ ያሠሩበት፥ የካቢኔ ቦታዎችን የተቆጣጠሩበት መንገድ፥ ጓደኞቻቸዉን ለፍርድ ማቅረብ አለመፈለጋቸው፣ በአዲስ አበባ የሚደረገው መታወቂያ እደላና የለገጣፎዉ ዘርን ያማከለ ማፈናቀል ሲታይ አዲሶቹ መሪዎች በመሰረታዊ ደረጃ ያንኑ የኖርንበትን የዘር መዘውር እያሽከረከሩት እንደሆነ መገንዘብ ይቻላል።

አሁን ትኩረት እየተደረገበት ያለዉ ህዝቡን የሚያማልሉ ነገሮችን በማዉራት ከእለት ወደ እለት ስልጣንን እያጠናከሩ መሄድ ነዉ። በቅርቡ የቀረበዉ አንዱ ማደናገርያ ኢሕአዴግ ወደ አንድ ፓርቲ መቀየሩ ከጎሳ ፖለቲካን እንደሚያወጣን ተደርጎ የቀረበበት መንገድ ነዉ። ኢትዮጵያ ውስጥ ስራ ላይ ያለው ፌዴራሊዝም ለዜጐች እውቅና ያልሰጠ፥ ዜጋ ለመሆን ቅድሚያ የጐሳ አባልነትን የሚጠይቅና ብሔር ብሔረሰቦች የሚል ስም የወጣላቸው ጐሳዎች ራሳቸውን በራሳቸው የማስተዳደር እስከ መገንጠል መብት የሚሰጥ ነው። ይህ አይነት የአስተዳደር መዋቅር በጐሳ የተደራጁ ፓርቲዎችን መኖር ግድ ይላል። አንድ የፖለቲካ ድርጅት ከጐሳ ወደ አገራዊ አወቃቀር እቀየራለሁ ሲል እንዴት አድርጐ አልደራደርበትም የሚለውን የጐሳ ፌዴራሊዝም እንደሚያስቀጥለው ግልፅ አይደለም። የጐሳ አደረጃጀት ለዚህ የፌዴራል ስርአት አንቀሳቃሽ ሞተር ነው። ይህ የጐሳ ፌዴራሊዝም ያለጐሳ አደረጃጀት አንድ ኢንች መጓዝ አይችልም።

ጠ/ሚ ዐቢይና ቡድናቸዉ እውነት እንደሚያወራውና እንደሚወራለት የኢትዮጵያዊነት ስሜት ካለው ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባው ይህንን ፀረ-ሰብ የሆነ መርዝ ህገ መንግስት ለመቀየር ጥረት ማድረግ ነው። ይህ ሳይሆንና የራሱን ፓርቲ በዘረኝነቱ እፀናለሁ እያለ ኢሕአዴግ የሚባለውን ሙት ድርጅት በብቃት ላይ የተመሰረተ አገራዊ ፓርቲ አደርገዋለሁ የሚለው ፉከራ በመርህም ሆነ በተግባር ትርጉም የማይሰጥ ነው። አገራዊ ፕሮግራም ያላቸው ተቃዋሚ ፓርቲዎች አገራዊ ፕሮግራም ይዘው የሚንቀሳቀሱት ሥልጣን ቢይዙ ይህንን የጐሳ ፌዴራሊዝም እንቀይረዋለን ከሚል እምነት በመነሳት እንጅ ይህን የጐሳ ፌዴራሊዝም በአገራዊ የፖለቲካ ፕሮግራም ልንመራው እንችላለን ከሚል እምነት አይደለም። ይህ ሊሆን እንደማይችል ያውቁታል። አንድ ስልጣን ላይ ያለ ፓርቲ ግን ከፈረሱ በፊት ጋሪውን አስቀድማለሁ ቢል ባዶ ቅጥፈት ከመሆን አያልፍም። ኢህዴግን ለስሙ አንድ ፓርቲ ነው ብሎ ማወጅ የሚቻል ቢሆንም ይህ የጐሳ ስርአት እስካለ ድረስ ውስጣዊ አደረጃጀቱ ጐሳዊ ባህርይውን እንደያዘ ይቀጥላል። ትግራይን በትግሬዎች፥ አማራውን በአማራና ኦሮሙውን በኦሮሞ ብቻ አስተዳድር የሚለው የፌዴራል ስርአት አወቃቀር የግድ ከላይ የዳቦ ስም ቢያወጡለትም ውስጣዊ ጐሳዊ አደረጃጀታቸውን ይዘው እንዲቀጥሉ ያስገድዳቸዋል። ለዚህ ነው የዶ/ር አብይ የጐሳ ፌዴራሊዝም ሳይነካ ኢህአዴግን አንድ አገራዊ ፓርቲ አደርጋለሁ የሚለው ቃል አገሪቱ ከገባችበት አዙሪት ለመዉጣት አቅም የሚያንሰው።

ይህ የለዉጥ ሁኔታ ውልና አቅጣጫ የሌለዉ በመሆኑ አገሪቱ ወደ አጠቃላይ ቀዉስ እያመራችና የዘር ማፅዳቱ ሂደት በየአካባቢው እየቀጠለ ይገኛል። አገዛዞች በተቀያየሩ ቁጥር ራሳቸዉን እንደፃድቅ እየቆጠሩ ያለፉትን ስርአቶች ስህተት መድገማቸዉን ቀጥለዋል። እነሱ ቤተ መንግስቱን ሲቆጣጠሩት እራሳቸዉን እንደ ብፁእና ጥፋት እንደማይመጣባቸዉ አድርገዉ ያስባሉ። በቅዱስ መፅሃፍ የተገለፀ አንድ ታሪክ ሁኔታዉን ይገልፀዋል። አስቴር በቤተ መንግስት እየኖረች አይሁዳውያን እንዲጠፉ የሚያዝዘው አዋጅ ሲወጣ መርዶክዮስ ይህ አዋጅ እንዲሻር ንጉሱን ገብታ እንድታናግር ሲጠይቃት በማመንታቷ ” በንጉሥ ቤት ስለ ሆንሁ ከአይሁድ ሁሉ ይልቅ እድናለሁ ብለሽ በልብሽ አታስቢ። በዚህ ጊዜ ቸል ብትዪ ዕረፍትና መዳን ለአይሁድ ከሌላ ስፍራ ይሆንላቸዋል፥ አንቺና የአባትሽ ቤት ግን ትጠፋላችሁ፤ ደግሞስ ወደ መንግሥት የመጣሽው እንደዚህ ላለው ጊዜ እንደ ሆነ ማን ያውቃል?” የሚል መልእክት ላከባት። ዶ/ር አብይና ቡድናቸዉ ወደ ስልጣን ሲመጡ የኢትዮጵያ ህዝብ የደገፋቸው ወያኔ ካመጣብን ዘረኝነትና የመበተን አደጋ ያድኑናል ከሚል እምነት ነበር። እየሆነ ያለው ግን ተቃራኒው ነው። አሁንም በዘር ተቧድነው ቤተ መንግስቱን ተቆጣጥረው የወያኔን ስግብግብነት እያስናቁት ይገኛሉ።

በአንደበት ስለ አንድነት እየተሰበከ በተግባር ግን ፊንፊኔ ኬኛ እያሉ በዘር ፌዴራሊዝም አልደራደርም ይላሉ። አገሩ እየፈራረሰ መሆኑን አይኑን ከፍቶ ለሚያይ ሰው ግልፅ ነው። የሚያሳዝነው እነ ዩጐዝላቭያን የበተነው የጐሳ አስተዳደር የእኛ የሚሉትን ህዝብ ጥቅም ያስጠብቅልናል ብለው ሙጭጭ ማለታቸው ነው። ያልገባቸው ነገር በዚህ የጐሰኝነት አዋጅ ማንም አትራፊ አይኖርም። ዛሬ ቤተመንግስቱን ስለያዙ ከጥፋት እድናለሁ ብለው ማሰብ አይገባቸዉም። እነሱም ሆኑ እወክለዋለሁ የሚሉት ህዝብ ከሚመጣው ጥፋት አይድንም።

በተለይ በኢትዮጵያዊነቱ ብቻ ተማምኖ ነገሮች ከዛሬ ነገ ይለወጣሉ በሚል በጎሳ ባለመደራጀት የሚጠብቀዉ ማህበረሰብና በአክራሪ ብሄርተኞች ጨቋኝ ነዉ ተብሎ የተፈረጀዉ ለረጅም ዘመን በጎሳ ሳይደራጅ የቆየው የአማራዉ ማህበረሰብ ለዘር ማፅዳት የተጋለጡ ናቸዉ። ለአክራሪ ብሄረተኞች የሚያደላ ህገ መንግስትና መዋቅር እንዲሁም ይህ ነዉ የሚባል የረባ ጠንካራ ተቃዋሚ ፓርቲ አለመኖሩ እነዚህን የማህበረሰብ ክፍሎች ለከፋ አደጋ እንዲጋለጡ አድርጓል። በዚህ ከፋፋይ ህገ መንግስት ላይ ቆመን ዴሞክራሲና የተረጋጋ አገር ይኖረናል ማለት የህልም እንጀራ ከመሆን አያልፍም። ለዚች አገር መረጋጋትና እድገት የሚበጀዉ ከዚህ የጎሳ ፌዴራሊዝም ተላቀን የዜጎችን መበት፥ አገራዊ አንድነትንና የዘዉጌዎችን ባህላዊና እራስን በራስ ማስተዳዳር የሚያስችል አዲስ ህገ መንግስታዊ ስርአት መመስረት ሲቻል ነዉ። ይህ የማይቻልና ሁኔታዎች በዚህ የሚቀጥሉ ከሆነ ግን ሁሉም ራሱን ለመከላከል በየጎሳው የመደራጀቱ ሂደት በፍጥነት እየቀጠለ ይሄዳል ማለት ነዉ።

ይህ ዘረኛ የጎሳ አስተዳደር በስራ ላይ እስካለ ድረስና ምንም አይነት መሰረታዊ የፖሊሲ ለዉጥ ሳይደረግ በአንደበት በሚነገሩ ነገሮችን ብቻ ተማምኖ መዘናጋት በቡራዩ፥ ለገጣፎ፣ ጌዶኦ፥ ወልቃይት፥ ድርዳዋ፥ አዋሳና ሌሎች ቦታዎች እንዳየነዉ ዘርን መሰረት ላደረገ መፈናቀልና ዘር ማፅዳት መጋለጥ ይሆናል። አሁን ያለዉን አሳሳቢ ሁኔታ ለመለወጥና ምናልባትም እያንዣበበ ያለዉን ጥፋት ለማስቀረት ሁሉም ያዋጣኛል ብሎ በሚያምንበት አደረጃጀት በቁርጠኘነት መታገል ይኖርበታል። ከዳር ቆሞ ዘር ለገበሬ ነዉ እያሉ መዘናጋት ለአክራሪ ብሄረተኞች የዘር ማፅዳት ወንጀል ሲሳይ መሆን ነዉ።

Check Also

AMHARA FANO in London at Ethiopian Embassy

የዲያስፓራ መንገደኞች የሚያጋጥማቸው መከራ!

በቦሌ አየር ማረፊያ በፍተሻ እና ጥበቃ አካላት ተጓዦች ላይ የሚፈፀም ውንብድና እና ዝርፊያ! ድርጊቱ የተፈፀመው …

Multi threaded Redundant Dedicated Server in USA and in Europe.