Breaking News
Home / Amharic / የዓይን ምስክር ነኝ። አንዱ ዓለም ተፈራ!

የዓይን ምስክር ነኝ። አንዱ ዓለም ተፈራ!

የትግራይ ሕዝብ ነፃ አውጪ ግንባር ለመጀመሪያ ጊዜ ተከዜን ተሻግሮ ወደ ወልቃይት ሲገባ፤ በቦታው ነበርኩ። ለምን እንደገባና ገብቶ ምን እንዳደረገ የነበረውን ሀቅ ከተረዳን፤ ዛሬ በቦታው መደረግ ስላለበት የአስተዳደር ውሳኔ፤ ትክክለኛ ግንዛቤ ይኖረናል። የዚህ ጽሑፍ መልዕክት ይሄው ነው።

የዛሬ አርባ ዓመት፤ የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ሠራዊት፤ ወልቃይትን ተቆጣጥሮ፤ ሕዝቡ ራሱን አደራጅቶ እንዲያስተዳድር አድርጎ ነበር። ይህ አካባቢ ከአራቱ በቤጌምድርና ስሜን ክፍለ ሀገር ካሉት ዞኖች አንዱ ነበር። የወልቃይት ወይንም አራተኛው ዞን ተብሎ ይጠራ ነበር። በኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ) የሚመራው ይህ ሠራዊት፤ እያንዳንዳቸው በሶስት ቡድኖች የተደራጁ፣ ሶስት ኃይሎች ነበሩት። የጠቅላላ ታጋዮች ድምር ቁጥር፡ ወደ አንድ መቶ ሃምሳ ይጠጋ ነበር። በወቅቱ በበለሳ ያለው የዞን ሁለት ክፍል ላቀደው የጥቃት ዘመቻ ዕርዳታ ስለጠየቀ፤ ሁለቱ የወልቃይት ኃይሎች ወደዚያ ተልከው ነበር። በቀሪው ኃይል የነበሩት ሶስቱ ቡድኖች፤ አንደኛው ክፍል ወደ ቆላው ወርዶ፣ መዘጋ ባለው መሬት እንዲንቀሳቀስ ተመደበ። ሁለተኛው ቡድን እዚያው ደጋው ላይ በደቡብ በኩል፤ ወደ ጠለሎ እንዲሄድና የጠገዴን ሁኔታ እንዲከታተል ተመደበ። እኔ የነበርኩበት ሶስተኛው ቡድን፤ አሁንም በደጋው ምዕራብ በኩል፤ ወደ ቀብትያ በመሄድ፤ ከዚያ ሆኖ ከጎንደር ወደ ሁመራ በሚወስደው መንገድ ያለውን የደርግ ወታደራዊ እንቅስቃሴ እንዲከታተል ተመደበ። እኔ የዚህ ቡድን የፖለቲካ ኃላፊ ነበርኩ።

የኛ ቡድን፤ የቀብትያ ዋና ከተማ አዲ ሕርፃን ደረስን። በዚያ ትንሽ ቅይታ ካደረግን በኋላ፤ ወደ ምዕራብ የደጋው ጫፍ በመሄድ፤ ቁልቁል የቆላውን መሬት ከምናይበት ቦታ ደረስን። እግረ መንገዳችን ሾኔ የሚኖሩቱን ፊታውራሪ የሺወንድም አግኝቼ አነጋግሬያቸው ነበር። የደጋው ጫፍ ስንደርስ አንድ አራት ጓዶችን የያዘ ቡድን ወደ ቆላው ወርዶ፤ በሃከር አካባቢ ተጠግቶ፤ በዚያ የሰፈረውን ጦር ወታደራዊ እንቅስቃሴ እንዲከታተል ላክን። ሌሎቻችን በዚያ አካባቢ እንደምንጠብቃቸው ተነጋግርን። በስተሰሜን የተከዜ ወንዝና ኤርትራ፣ በስተምዕራብ ቆላውና በሩቅም የሱዳን ምድር ተንጣሏል። ከከብት ጠባቂ ወጣቶች ጋር እየተነጋግርኩ ባለሁበት ወቅት፤ አንድ ያካባቢው ነዋሪ ተጠጋኝና፤ “አያ ጓዱ! በስተአዲ ረመጥ የሚነፍሰው ጥሩ አይደለም!” አለኝ።

ከእረኞቹ ለይቼ ወደ ጎን ወሰድኩና፤ “ምንድን ነው?” ብዬ ጠየኩት። “ኧረ! እቺ የከብት ሌባ አዲ ረመጥ ገብታለች። ደሞ በጣም ብዙ ናት! ሁለት በጣሊዎን ናት! ገበያ ውዬ መምጣቴ ነው።” አለኝ። ያካባቢው ሕዝብ ለኛ ያለውን ፍቅር ስለማውቅ፤ ያለ ምንም ሌላ ጥያቄና መልስ፤ አመስግኜ አሰናበትኩት። በእረኞች በኩል መልዕክት ቆላ ለወረዱት ተልኮ፤ የቡድኑን አባላት ጓደችን በመሰብሰብ ስለሁኔታው ገለጥኩላቸው። በቀጥታ ወደ መዘጋ ወርደን፤ በወልቃይት ካሉትና ጠለምት ካሉት የሠራዊቱ አባላት ጋር ግንኙነት መፍጠር እንዳለብን ተረዳን። የአሁኑ ተልዕኳችን ይህ እንደሚሆንና፤ ወደ ቆላው የተላኩት ጓዶች፤ ወደ ደጋው ሳይወጡ፤ በሰሜን በኩል ቆላውን ይዘው በአዲ ጎሹ በኩል ወደ መዘጋ በመምጣት እንደሚያገኙን ተወስኗል። ወዲያው ተሰባስበን፤ በቀጥታ ወደ አዲ ሕርፃን የሚወስደውን መንገድ ትተን፣ በደቡብ በኩል ዳር ዳሩን በመጓዝ ከከተማው ለመግባት ወሰን። ከፊት ትግርኛ ተናጋሪ የሁኑ ሁለት ፈታሽ ጓዶችን አስቀድመን፤ ዝርዝር በማለት በፍጥነት ተጓዝን። አዲ ሕርፃን ደቡብ ምዕራብ ጫፍ ላይ ቀጥ ብሎ የወጣ አንድ ኮረብታ አለ። ሁላችንም አጣጥፈን በመታጠቂያን ላይ በጀርባችን የያዝናትን የመኝታ ልብሳችንን አውጥተን፤ እንደ አገሩ ሰው ነጠላ ለብሰናል። ጠመንጃዎቻን በዚችው ጨርቃችን ሸፍነናል። አንድ ግሬኖቭ ዲ ነበረንና እሱን መደበቅ ስለማይቻል፤ በመጨረሻ ከቡድኑ ወታደራዊ መሪ ኋላ ሆኖ፤ በትከሻው እንዲይዘው ተደርጓል። አንድ ማስ ጠመንጃ የያዘ ጓድ፤ ከመትረየሱ ኋላ ተመድቧል።

በዚህ የመስመር አሰላለፍ ስንገሰግስና ወደ አዲ ሕርፃን ስንጠጋ፤ “ጠጠው በል!” – ቁም ማነህ! የሚል ትዕዛዝ ከኮረብታው ላይ ተሰማ። ከፊት የነበሩት ጓዶች፤ የአጠቃላዩን ሁኔታ ስለተረዱ፤ የከብት ሌባዋ እዚህ እንደደረሰች አወቁ። “ንእና ኢና!” – እኛ ነን! በማለት አዘናግተው፤ ወደኋላ ላለነው ምልክት ሠጡን። በያለንበት ቁጭ አልን። እነሱ በቀስታ ወደኋላ መጥተው ወደኛ ሲጠጉ፤ ትንሽ ወደኋላ ተመልሰን ወደ ዘባጣው ገብተን፣ ራቅ ብለን ወደ አዲ ሕርፃን የሚወስደውን የመኪና መንገድ አቋርጠን ወደ ሾኔ አመራን። አሁን ፍጥነታችን ጨምሯል። ጥንቃቄ የሰዓቱ ጥሪ ነው። አስልተን ወደ ፊታውራሪ የሺወንድም ቤት ተጠጋን። ጠባቂዎችን አስቁመው ስለነበር፤ ሰላም መሆኑን አረጋገጥን። እሳቸው ሲያዩን ደስታቸው በጣም ጥልቅ ነበር። “እንኳን መጣህ! ካባቴ ጋር ልጅ ሆኜ ጣሊያንን እዚህ ሳናስገባ ተዋግተናል። ይሄ የቆላው ጥቅጥቅ ጫካ አለልን! እንኳን የናንተን መሣሪያ ይዘን፤ በጥቂት ነፍስ ወከፍ ነበር ጣሊያንን ያጠቃነው!” በማለት የሳቸውን ዕቅድ ደረደሩልን። እኔም ተልዕኳችን ሠራዊቱን ማግኘትና ሁኔታውን እኛም ማስረዳት ከነሱም መረዳት እንደሆነ ገለጥኩላቸው። እሳቸው ግን አይሆንም አሉ። ዘመዶቻቸውን አሰባስበው ሠራዊት እንደሚያቋቁሙና እኛ ከፍተኛ ሚና እንዳለብን ነገሩኝ። አንድ ቀን የግድ አሳደሩን። በበነጋታው ግን፤ እንደማያቆሙን ሲረዱ፤ ሸኚ መድበው በሰሜን በኩል ቆላ ወርደን፤ ብላምባ ላይ ወደ ደጋው ወጥተን በበሩ በኩል ወደ መዘጋ እንደምንወርድና ጓዶችን እንደምናነጋግር፤ የሳቸውንም ሁኔታ እንደምናስረዳላቸው ነግረናቸው ተሰናበትን።

ደጋው ደርሰን ከማውቃቸው ሰው ቤት ስጠጋ፤ ተደናግጠው ወጥተው፤ “ኧረ ታስፈጁናላችሁ! ቶሎ ይሄን ቦታ ልቀቁልን! በዚህ እኮ ነው የመጡትና የሚተላለፉት!” በማለት የድንጋጤና የፍርሃት ሁኔታቸውን ነገሩኝ። ሴቶቹን ቶሎ ምግብ አዘጋጅተው እንዲሠጡን አዘዙልን። ሴቶቹ “ዚአቶምስ . . . ” እኒህስ የኛዎቹ ናቸው – አሉና ምግብ ለማዘጋጀት ተጣደፉ። ትልቋን ሴትዮ ቀረብኩና፤ “ምን ሆነ?” አልኳቸው። “ኧረ! ምኑን ብየህ!” ብለው ባጭሩ አስቀመጡልኝ። ካዚያ ቀን በፊት በነበረው ዕለት ስብሰባ ገበያ ላይ ጠሯቸው። በስብሰባው የነገሯቸው፤ ከዚያች ዕለት ጀምረው ትግሬዎች እንደሆኑ፣ አማራ ትግሬነታቸውን እንደቀማቸው፣ ከዚያች ዕለት ጀምረው በትግርኛ ማልቀስና መዝፈን እንዳለባቸው፣ አቤቱታቸውን ጽፈው ለነሱ ማቅረብ እንዳለባቸው አዋጅ ነገሯቸው። እሳቸውም ለኔ፤ “እና ማን እኛን ምን እንደሆን ነግሮን ያውቃል! ደሞሳ እኛ ራሳችንን የማናውቅ ሆነን ነው እነሱ ሚነግሩን! በማንውቀውስ ይትባሕል እንዴት አርገን ነው የምንዘፍነውና የምናለቅሰው! ኧረ ጉድ ነው! መንግሥት ተሆኑ ደርግን አቸንፈው ከተማ ይግቡና ግብሩን እንልክላቸዋለን እንጂ፤ ተኛ መሃል ገብተው ይሄን አርጉ ያን አታድርጉ ምንድን ነው!” ብለው ምሬታቸውን ገለጡልኝ።

በጠለምትና በራያ የሆነውም ይሄው ነው። በሁለተኛው ቀን፤ በለሳ የሄዱት ኃይሎች ተመልሰው ሸረላ ላይ ከባድ ጦርነት አደረግን። አሰላለፉ አንድ ከአስር በላይ ነበር። በኛ በኩል አንድ መቶ ስድሳ የሚሆን ሲሰለፍ በትግራይ ሕዝብ ነፃ አውጪ ግንባር በኩል ከሁለት ሺህ በላይ ነበር። ጦርነቱን አቸናፊ ሳይኖርበት መሽቶ ሁለታችንም በያለንበት ቆምን። ስለ ጦርነቱና የአሰላለፍ ስልታቸው በሌላ ጊዜ እመለስበታለሁ። ባጭሩ፤ ከኛ በኩል አስራ ሰባት ቁስለኞች ነበርን። የሞተ አልነበረብንም። እኔ ከባድ ቁስ ከደረሰባቸው አንዱ ነበርኩ። አሁንም ሰባራ የቀኝ ክንድና ሰባራ የአጥንት መጋጠሚያ ይዤ እኖራለሁ። ከነሱ በኩል ሬሳቸውን ትተውት፤ የአካባቢው አራሾች ሬሳውን ማየት ስለከበዳቸው፤ ከሶስት ቀን ቆይታ በኋላ ሰማንያ አንድ እንደቀበሩ ነግረውኛል። በወልቃይት ካደረግናቸው ከባድ ጦርነቶች አንደኛው ይህ ነበር።

ከዚህ የተረዳሁት፤ ወልቃይት መግባታቸው የትግላቸው አካል እንጂ የሕዝቡ ወይንም የአስተዳደር ጉዳይ አይደለም። በየትኛውም ሕግ ተመርተው አይደለም። ሕዝቡን አስገድደው ትግሬ ለማድረግ ነው የዘመቱት። ይህ የሕገ-መንግሥት ጉዳይ አይደለም። በጉልበት የተወሰደ ቦታ ነው። ሁለተኛ ህዝቡ የኛ አላላቸውም። እኛን ሲያዩ፤ “እኒህስ የኛዎቹ ናቸው!” በማለት፤ ፍራቻቸውን ገልጠውልኛል። በአዋጅ ሕዝቡን ትግሬ፣ አካባቢውን የትግሬዎች ሊያደርጉ ነው ወልቃይት የገቡት። ከሁሉ የሚያስከፋው ደግሞ፤ ያካባቢውን ሕዝብ በመግደል፣ በማሰር፤ አስገድዶ አማራነቱን እንዲጥል በማድረግና አሳዶ ከአካባቢው በማስለቀቅ መሬቱን ወደ ትግራይ አጠቃለዋል። ከመሬቱ ጥቅም ጋር የተያያዘው የፖለቲካ ውሳኔያቸው፤ የሱዳን በርነቱና የመሬቱ ለምነት ዋናዎቹ ናቸው። ከትግራይ እየመጡ የሚሠሩና ገንዘባቸውን ይዘው ወደ ትግራይ የሚመለሱ ትግርኛ ተናጋሪዎች በየጊዜው መመላለሳቸው፤ በአካባቢው ትግርኛ እንዲነገር ረድቷል። ይሄንን መሠረት አድርገው ነው የትሕነግ መሪዎች ሕዝቡን ትግሬ፣ መሬቱን የትግራይ ለማድረግ የጣሩት።

ምን ጊዜም ቢሆን አንድን አካባቢ ለማስተዳደር፤ ሕገ-መንግሥቱ በሚፈቅደውና ሕዝቡና ፓርላማው በሚስማማበት መንገድ ማዋቀር ይቻላል። የወልቃይት፣ የጠገዴና የራያ አወቃቀር ከዚህ የተለየ ነው። እኔ የአማራ ወይንም የትግሬ መሬት የሚለው ትርጉም አይሠጠኝም። መሬቱ የኢትዮጵያ ሆኖ፤ የቀደም ነዋሪዎቹ ንብረት ነው። ሁሉም ባለቤት ነዋሪዎች መሬታቸውን ተነጥቀዋል። ከፊሎቹ ተገድለዋል። ከፊሎቹ ታስረዋል። ከፊሎቹ ተሰደዋል። ባለቤትነታቸውን ግን የሚሰርዝ ሕግም ሆነ አግባብ የለም።

በኔ እምነት፤ መልስ የሚሆነው፤ አገራችንን በጋራ አሁን ሕዝቡ እንደታደጋት ሁሉ፤ ባለቤትነቱንም በጋራ የምናደርግበት ሕገ-መንግሥት እንዲኖር ነው። ኢትዮጵያዊነት ወሰን የለውም። ኢትዮጵያዊና ኢትዮጵያዊት የትም ቦታ ኢትዮጵያዊነታቸው ነው ምልክታቸው። በኢትዮጵያዊነታቸው የትም ሊኖሩ ይገባል። የትግራይ ሕዝብ ነፃ አውጪ ድርጅት ያስቀመጠው የክልል አስተዳደር የኢትዮጵያዊነት ጠር ነው። የተለየ የአስተዳደር መዋቅር ሊዘረጋ ይገባል፡፡ የአገራችን አንድ መቶ አስር ሚሊዮን ሕዝብ፤ በአስራ አንድ ክፍለ አገራትና በአንድ መቶ አስር አውራጃዎች ሊስተዳደር ይችላል። እያንዳንዱ አውራጃ አንድ ሚሊዮን ሕዝብ እንዲኖርበት፤ የሕዝቡን እንቅስቃሴ፣ የገበያውን ሁኔታ፣ የመልክዓ ምድሩን አቀማመጥና ኩታ ገጠምነት በሚመለከት ሊጠናና ሊዋቀር ይችላል። ክልል የአስተዳደር አመቺ መዋቅር እንጂ፤ ከማንነት ጋር የተያያዘ መግለጫ አይደለም። ማናችንም ብንሆን የምንስተዳደረው በኢትዮጵያዊነታችን እንጂ ከወላጆቻችን በወረስነው የደም ምንጭ መሆን የለበትም። አለዚያማ ኢትዮጵያዊነታችንና ጀግኖች የሕዝቡ ፋኖና ወታደሮች ትግራይ ውስጥ የከፈሉት መስዋዕትነት የማን ተብሎ ሊፈረጅ ነው!

እዚህ ላይ መልሱ ያለው ከሕገ-መንግሥቱ ላይ ነው። ሕገ-መንግሥቱ ደግሞ ሁሉን ገዥ ሰነድ ነው። ይህ ሰንድ የያዛቸው ብዙ ጉዳዮች አሉ። አሁን አገራችን የምትስተዳደርበት ሕገ-መንግስት፤ ያለ ምንም ጥያቄ የትግራይ ሕዝብ ነፃ አውጪ ግንባር ሕገ-መንግሥት ነው። በውስጡ ጥሩ ነገሮች የሉት ማለት አይደለም። አሉት። መሠረታዊ ሂደቱና ግቡ ግን፤ የዚህን የትግራይ ሕዝብ ነፃ አውጪ ግንባር ዓላማ ማሟላት ነው። ለውጡ ግቡን የሚመታው ይሄን ሕገ-መንግሥት ትክክለኛ አለመሆን መቀበልና በዚህ ላይ ለውጥ እንደሚያስፈልግ አምኖ፤ ይሄን ለመተግበር መንገድ ሲጀመር ነው። የዓይን ምስክር ነኝ።

Check Also

AMHARA FANO in London at Ethiopian Embassy

የዲያስፓራ መንገደኞች የሚያጋጥማቸው መከራ!

በቦሌ አየር ማረፊያ በፍተሻ እና ጥበቃ አካላት ተጓዦች ላይ የሚፈፀም ውንብድና እና ዝርፊያ! ድርጊቱ የተፈፀመው …

Multi threaded Redundant Dedicated Server in USA and in Europe.