Breaking News
Home / Amharic / ከአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ የተሰጠ መግለጫ !

ከአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ የተሰጠ መግለጫ !

የሕዝባችንን ሰላምና ደኅንነት የማስጠበቅ ኃላፊነቱን መንግስት በአግባቡ ሊወጣ ይገባል!

ሰሞኑን በአማራ «ክልል» በማዕከላዊ ጎንደር ዞን ጭልጋ አካባቢ በተፈጠረ ግጭት በደረሰው የሰው ሕይወት መጥፋትና የንብረት መውደም የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ–አብን የተሰማውን ጥልቅ ኃዘን እየገለፀ ለተጎጅ ቤተሰቦች መፅናናትን እንመኛለን፡፡ አብን እስካሁን በደረሰው መረጃ መሰረት ከ50 በላይ ቤቶች ተቃጥለዋል፤ በርካቶች ቆስለዋል፡፡ እንዲሁም ውድ የሆነው የሰው ሕይወት አልፏል፡፡ ከሌላ አካል ተልዕኮ ተቀብለው በመጡና ራሳቸውን በቅማንት የማንነት ኮሚቴ ስም ባደራጁ እና ይሄን የጥፋት ተልዕኮ ተሸክመው በአማራ «ክልል» በሚገኙ የመንግሥት ተቋማት በሚሰሩ ግለሰቦች በአማራ ሕዝብ ላይ የተፈፀመ ጥቃት ከመሆኑም ባሻገር የቅማንት የማንነት ጉዳይ በክልሉ ምክር ቤት ተመልሶ ያደረና የመጨረሻ እልባት የተሰጠው በመሆኑ በሕዝባችን ላይ በተደጋጋሚ ጥቃት ሊያስፈፅም የሚችል ነገር አለመኖሩን አብን ያምናል፡፡ የፌደራል መከላከያ ሰራዊትም ግጭቱ በተከሰተበት አቅራቢ ቢኖርም ለሕዝባችን ተገቢውን ከጥቃት የመከላከል እርምጃ እየወሰደ አይደለም፡፡

ስለሆነም የ«ክልሉ»ም ሆነ የፌደራል መንግስት በሕዝባችን ላይ በተደጋጋሚ የሚፈፀመውን ጥቃት የማስቆምና የሕዝባችንን ሰላምና ደኅንነት የማስጠበቅ ኃላፊነቱን በሚገባ ሊወጣ ይገባል፡፡ በድርጊቱ ፈፃሚዎችና ጠንሳሾች ላይም የማያዳግም እርምጃ እንዲወሰድ አብን እየጠየቀ መላ ሕዝባችን ከመቼውም ጊዜ በላይ አንድነቱን በማጠናከር መሰል በኅልውናው ላይ የሚፈፀሙ ጥቃቶችን ለመመከት ዝግጁ ሆኖ እንዲጠብቅ አብን ያስገነዝባል፡፡

የፌደራልና የ«ክልሉ» መንግሥት የሕዝባችንን ሰላምና ደኅንነት ለማረጋገጥ በሚያደርጉት ጥረት በሙሉ አብን ሙሉ ድጋፍ እንደሚያደርግ እየገለፅን ይህ ሳይሆን ቀርቶ ግን በሕዝባችን ላይ የሚፈፀመውን ጥቃት መንግሥት ማስቆም ካልቻለ አብን መላውን አማራ በማንቀሳቀስ ራሱን የመከላከል ተፈጥሯዊ መብቱን እንዲጠቀም የሚያደርግ መሆኑን እንገልፃለን፡፡ በድጋሚ ለተጎጅ ቤተሰቦች መፅናናትን እንመኛለን።

አንድ አማራ ለሁሉም አማራ፥ሁሉም አማራ ለአንድ አማራ!

ኅዳር 26/2011 ዓ/ም
የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ
አዲስ አበባ ፣ ሸዋ ፣ ኢትዮጵያ

Check Also

AMHARA FANO in London at Ethiopian Embassy

የዲያስፓራ መንገደኞች የሚያጋጥማቸው መከራ!

በቦሌ አየር ማረፊያ በፍተሻ እና ጥበቃ አካላት ተጓዦች ላይ የሚፈፀም ውንብድና እና ዝርፊያ! ድርጊቱ የተፈፀመው …

Multi threaded Redundant Dedicated Server in USA and in Europe.