Breaking News
Home / Amharic / ሁለት መንግስት ባለበት ሀገር እንዴትነዉ ፍትህ የሚኖረዉ?

ሁለት መንግስት ባለበት ሀገር እንዴትነዉ ፍትህ የሚኖረዉ?

ፍትሕ ያጣ ሕዝብ ፍትሕን በእጁ ይፈልጋል፤ ይህ እንዳይሆን ደግሞ መንግሥት ወንጀል የሚሠሩ አካላትን ወደሕግ ማቅረብ አለበት፡፡” ምሁራን

ባሕር ዳር፡ ጥቅምት 24/2012 ዓ.ም (አብመድ) ፍትሕ ያጣ ሕዝብ ስለፍትህ ሠላማዊ ሰልፍ ይወጣል፡፡ ድምጹን ከፍ አድርጎ ለመንግሥት ጥያቄ ያቀርባል፡፡ ልክ እንደ ኢትዮጵያ አስተዋይ የሆነ ሕዝብ ሲሆን መንግሥት አልሰማው ሲል ‹ቀን ይለፍ› ብሎም ይታገሳል፡፡ ያን ሁሉ ትዕግስት አይቶ መንግሥት ጥያቄውን መመለስ ካልቻለና ፍትሕ ካላሰፈነ ያን ጊዜ ሌላ አማራጭ ይፈለጋል፡፡ ሕዝብ ፍትሕን በእጁ ይፈልጋል፤ ድንጋይ ይወረውራል፤ ጥይት ይተኩሳል፤ ነፍስ ያጠፋል፤ አካል ያጎድላል፡፡ ይህ የሚሆነው ፍትሕ ሲጠፋ ነው፡፡ አንዱ በማን አለብኝነት ሰው ሲገድል ሌላኛው ሁሌም ሙሾ አውራጅ ከሆነ ያን ጊዜ ትክክለኛውን ፍትሕ በእጁ ወደማግኘት ይሄዳል፡፡

በኢትዮጵያ አሰቃቂ የሆነ የሰበዓዊ መብት ጥሰት መፈጸሙ የዕለት ከዕለት ዜና እየሆነ መጥቷል፡፡ በቅርብ ሳምንታት ብቻ ብዙዎች ሞተዋል፣ ገሚሶች አካላቸው ጎድሏል፡፡ ቁጥራቸው የብዙ ንጹኃን ዜጎች ደግሞ ቤትና ንብረታቸውን አጥተዋል፡፡ ይህን የተለመደ የሚመስል ድርጊት እንዴት መፍታት ይቻላል? በተለይ ግጭትና ብሔር ተኮር ጥቃት ቀስቃሾችን በዓለማቀፍ ፍርድ ቤት ጭምር መጠየቅ አይቻል ይሆን? ሲል አብመድ ምሁራንን ጠይቋል፡፡

የሕግ ባለሙያና የሰበዓዊ መብት ተከራካሪ አቶ አለለኝ ምሕረቱ ‹‹የጅምላ ግጭት፣ ግድያና ማኅበረሰብ የማይለይ ጥፋት ሲፈጸም ‹ያገባኛል› ያለ ሰው ሁሉ በቡድንም ይሁን በግል ጥፋተኞቹን ወደ ሕግ ማቅረብ ይገባዋል፤ በዓለማቀፍ ፍርድ ቤት ጭምር መክሰስ ይቻላል›› ይላሉ፡፡

በኢትዮጵያ በርካታ የሰበዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች እንዳሉ የተናገሩት አቶ አለልኝ የተመዘገቡና ሕጋዊ ፈቃድ ያላቸው የሰበዓዊ መብት ድርጅቶች ማንነትንና ሃይኖማትን መሠረት አድርገው ግጭት የሚቀሰቅሱና ጥፋት ያደረሱ ሰዎችን መክሰስ እንደሚችሉም ተናግረዋል፡፡ ባለሙያው የሰበዓዊ መብት ድርጅታቸው እንቅስቃሴዎችን እንደጀመረ በመግለጽ በግለሰብ ደረጃም ቢሆን በማኅበረሰብ ላይ የሚደርስን ጥቃት ለማስቆም፣ ካሳ ለማስካስ እና ጥፋተኞችን ወደ ሕግ እንዲቀርቡ ማድረግ እንደሚቻልም አመላክተዋል፡፡

‹‹ነገር ግን በወንጀል ለመጠየቅ ዓለማቀፋዊ ሕጎች የሚፈቅዱ ቢሆንም ሁሉም ሰው ችግሩ የራሱን ቤት እስኪያንኳኳ ስለሚጠብቅ በቶሎ እልባት እንዳያገኝ ሆኗል›› ነው ያሉት የሕግ ባለሙያና የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ፡፡ የሚሠሩበት የሰብዓዊ መብት ድርጅት አባላት ከተለያዩ ብሔር ብሔረሰቦች የተውጣጡ እንደሆኑ የገለጹት አቶ አለልኝ የገንዘብ ችግር እንዲህ ዓይነት ችግሮችን ለመሟገት እንቅፋት እንደሆነባቸውም አስታውቀዋል፡፡

“የሕግ የበላይነት በሀገሪቱ የለም” ያሉት አቶ አለልኝ ‹‹መንግሥት የሕግ የበላይነትን ለማስከበር አቅም አጥቷል፤ አቅም አላነሰኝም ካለ ደግሞ የኢትዮጵያን መበጣበጥ ይፈልጋል ማለት ነው›› ሲሉም በመንግሥት በኩል ያለውን ግራ አጋቢ ሂደት ገልጸዋል፡፡ የመንግሥት ተቀዳሚ ተግባር የዜጎችን ደኅንነት መጠበቅ መሆኑን ያመለከቱት የሕግ ባለሙያውና የሰበዓዊ መብት ተከራካሪው የዜጎችን ደኅንነት ማስጠበቅ ያልቻለ መንግሥት ስልጣን መያዝ እንደማይገባውም ተናግረዋል፡፡

መንግሥት አቅሙን በሕዝብ መገንባት ስለሚችል ውይይቶችንና ስብሰባዎችን ከሕዝብ ጋር ማድረግ እንደሚገባውም አቶ አለልኝ አመላክተዋል፡፡ የሕዝብን ጉልበት የያዘ መንግሥት ጥፋተኞችን በቀላሉ መቆጣጠር እንደሚችልም ነው የተናገሩት፡፡ ወንጀል የፈጸሙ አካላትን መንግሥት ለሕግ ማቅረብ እንዳለበት የጠየቁት አቶ አለልኝ “ፍትሕ ያጣ ሕዝብ ፍትሕን በእጁ ይፈልጋል፤ ይህ እንዳይሆን ደግሞ መንግሥት ወንጀል የሚሠሩ አካላትን ወደ ሕግ ማቅረብ አለበት” ብለዋል፡፡

የሕግ መምህርና አማካሪው ፕሮፌሰር ዲባባ ተስፋዬ ደግሞ ማንኛውም ጥፋት በሕግ መብራራትና መመዘን እንዳለበት አብራርተዋል፡፡ ድንበር የማይገድበው ዓለም ዓቀፋዊ ሕግ እንዳለ የተናገሩት ፕሮፌሰር ዲባባ ‹‹ተጠያቂው ማነው የሚለውን በመለዬት አጥፊውን አካል ሀገር የሚያስተዳድረውን መንግሥትም መጠዬቅ ይቻላል›› ነው ያሉት፡፡ ማሳቃዬትና ዘር ማጥፋት የፈጸመ ግለሰብም ይሁን መንግሥት ጥፋተኛ ሆኖ ከተገኘ በየትኛውም ዓለም ዓቀፋዊ ሕግ ምክንያት ማቅረብ እንደማይችልና ፍርድ እንደሚፈረድበትም ተናግረዋል፡፡ ‹‹ይሁንና ኢትዮጵያ ውስጥ እኩይ ተግባር በሰው ልጅ የፈጸሙ አካላት ተጠያቂ ባለመሆናቸው ችግሩ እንዲቀጥል ሆኗል፡፡ መንግሥትም እነዚህን አካላት ለሕግ ማቅረብ ካልቻለ አሁንም ሌሎች ገዳዮች እየተፈጠሩ ችግሩ ቀጣይነት ይኖረዋል›› ብለዋል ፕሮፌሰር ዲባባ፡፡

ከሁሉ አስቀድሞ ‹ሰው ቅዱስ ነው› የሚለውን ጽኑ ቃል የያዘ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ይሁን የውጭ ዜጋ የጥፋት ኃይሎችን ወደ ሕግ የማቅረብ መብት እንዳለውም አመላክተዋል፡፡ በኢትዮጵያ የሚገኙ የሰበዓዊ መብት ተሟጋቾችና የሕግ ባለሙያዎች ከአድርባይነት እንዳልወጡም አመላክተዋል፡፡ ይህን ችግር ለመፍታት በግላቸው ጥረት እያደረጉ ቢሆንም ያልተዳራጁ በመሆናቸው ችግሩን በቶሎ ማሳወቅና መፍታት እንዳልቻሉም አመልክተዋል፡፡

‹‹ዳኞችና ፖሊሶች አቅም አጥተዋል›› ያሉት ፕሮፌሰር ዲባባ የትኛውም አካል ችግር ይፍጠር‹ ሕግ ሕግ ነው› ብለው ከመያዝ ይልቅ ስለደረጃ ዕድገትና ዳቦ ነው የሚያስቡት፡፡ ችግሩን ለመፍታትም ሰው ክቡር ነው የሚል ትውልድ በመፍጠር በመንግሥት አካል ወንጀለኛን ያዝ ሲባል ስንት ልያዝ? የሚል ሳይሆን ለምን? የሚል ዳኛና ፖሊስ መፍጠር እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡ ፕሮፌሰር ዲባባ የሚፈቀድላቸው ከሆነም የሕግ ባለሙያዎችንና ፖሊሶችን በራሳቸው ወጪ ለማስተማር ዝግጁ እንደሆኑ ጭመር አስታውቀዋል፡፡

ከእሴት የወጣ ትውልድ እየተፈጠረ እንደሆነ ያመላከቱት ፕሮፌሰር ዲባባ ‹‹ትውልዱ ሕግን ረስቶ በሌላ ጉዳይ ተጠምዷል፡፡ ትክክለኛ ሕዝባዊ መንግሥት ካለ የሰው ሕይወት እንዳይጠፋ፣ ንብረት እንዳይወድም፣ አካል እንዳይጎድልና ዜጎች ከቀያቸው እንዳይፈናቀሉ መሥራት አለበትም ብለዋል፡፡ ለሕዝብ ሞትና እንግልት ምክንያት የሚሆኑ አካላትም ለሕግ እንዲቀርቡ ጠይቀዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ታርቆ ክንዴ

Check Also

AMHARA FANO in London at Ethiopian Embassy

የዲያስፓራ መንገደኞች የሚያጋጥማቸው መከራ!

በቦሌ አየር ማረፊያ በፍተሻ እና ጥበቃ አካላት ተጓዦች ላይ የሚፈፀም ውንብድና እና ዝርፊያ! ድርጊቱ የተፈፀመው …

2 comments

  1. Gizatu Mengesha Tessema መንግስት አቅም እንዳለው በሰኔ 15ቱ ጊዜ እኮ አሳይቶናል። አይደለም እንዴ? ለመሆኑ በመንግስት የሚጠበቅን ተራ ወንጀለኛ መንግስት ለህግ ለማቅረብ አቅም አጠረው ማለት እንዴት ይቻላል? ባይሆን መንግስት በሚፈለገው አካል ላይ ተጽእኖ ለመፍጠር በፈለገው ዘንድ ደግሞ ከለላ በማድረግ ብጥብጡን አጠናክሮ ወደፈለገው ደረጃ ለማድረስ ፍላጎት አለው የሚለው ትንታኔ ግን ትክክል ነው።

  2. ሙሁራኖች እንዲህ አሉ እንዲያ እያላችሁ የምትዘባርቁት ነገር ነው ያሰጠላኝ እኔ አሁን የምፈልገው 86 ሰው እንዲሞት እና ለአያሌ ሰዎች አካል ጉዳትና መፈናቀል ቀጥተኛ ተጠያቂ የሆነው ጃዋር በህግ ሳይጠየቅ የትኛውንም አይነት የመንግስት ፕሮፓጋንዳ አልሰማም በቃ መንግስት ካለ እያንዳንዱ አጥፊ በህግ ይጠየቅ አለበለዚያ

Multi threaded Redundant Dedicated Server in USA and in Europe.