Breaking News
Home / Amharic / የጎሳ ፌዴራሊዝምና የኢትዮጵያዊ ዜግነት መብት በኢትዮጵያ – አሰፋ ነጋሽ

የጎሳ ፌዴራሊዝምና የኢትዮጵያዊ ዜግነት መብት በኢትዮጵያ – አሰፋ ነጋሽ

የጎሳ ፌዴራሊዝምና የኢትዮጵያዊ ዜግነት መብት በኢትዮጵያ – አሰፋ ነጋሽ * (ሆላንድ – ጥቅምት 2006 ዓ. ም)

1

 

ክፍል ሁለት

Read more in PDF

በቅርቡ የአማራ ጎሳ ተወላጆችን መፈናቀል አስመልክቶ አስያየታቸውን ከሰጡ ግለሰቦች መካከል አፍቃሪ-ኦነግ የሆነው የኦሮሞ የጎሳ ብሄረተኛ ጃዋር መሀመድ ለአንድነት ጋዜጣ የአማራው ህዝብ ችግር ተቆቋሪ በመምሰል በሰጠው ቃለ መጠየቅ አማራው ከቤኒሻንጉል የተፈናቀለው በወያኔ ተንኮል እንጂ የጎሳ ፌዴራሊዝም ባመጣው ችግር ምክንያት አይደለም በማለት የጎሳ ፌዴራሊዝም ውጤት የሆነውን ችግር ለማስተባበል ሞክሮአል። ጃዋር የአማራው ህዝብ መፈናቀል ምክንያት የወያኔ መንግስት ተንኮል እንጂ የጎሳ ፌዴራሊዝም ፖሊሲ የፈጠረው ችግር አይደለም በማለት የጎሳ ፌዴራሊዝም የዜግነትን መብትና ማንኛውም ኢትዮጵያዊ በፈለገበት ክልል ሂዶ የመኖርና ህይወቱን የመምራት መብት እንዳለው አድርጎ ለማቅረብ ሞክሮአል። ይህ እጅግ ስህተተኛና የጎሳ ፌዴራሊዝምን አጥፊነትና ሀገር-አፍራሽነት፤ የጎሳ ግጭትና የጥላቻ ፈጣሪነት ለመካድና ለመሸፋፈን የሚደረግ ጥረት ነው። እንደ ጀዋር መሃመድ ያሉ የነጻይቱን ኦሮሚያ ሀገር መፈጠር የሚጠባበቁ የኦሮሞ ብሄረተኞችም ሆኑ በሀገር ቤት ተደራጅተው በሰላማዊ መንገድ የሚንቀሳቀሱት የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግሬስ (የአቶ ቡልቻ ደመቅሳና የዶክተር መረራ ጉዲና ድርጅቶች ተዋህደው የፈጠሩት የጎሳ ፌዴራሊዝም አራማጅ ድርጅት ነው) ድርጅቶች፡ እንደዚሁም ሌሎች የጎሳ ፖለቲካ አራማጆች ይህ ዛሬ በወያኔ ትግሬዎች መንግስት ስራ ላይ የዋለው የጎሳ ፌዴራሊዝም ስርዓት በመጨረሻ ኢትዮጵያን በጎሳ ወደሚበታትንንና የሚመመኙትን ነጻ ኦሮሚያን፤ ኦጋዴንያን፤ ወዘተ ምስረታ ሂደት እያመራ መሆኑን ጠንቅቀው ያውቃሉ። በጎሣ ማንነት ላይ የተመሰረተው የጎሳ ፌዴራሊዝም ስርዓት የግለሰብን መብትና ነጻነት የዲሞክራሲያዊ ስርዓት መገለጫ አድርጎ ስለማያይ፤ እንዲያውም ይህንን የግለሰብ መብት ስለሚጻረርና ከግለሰብ መብት በፊት የቡድንን መብት ስለሚያስቀድም በተፈጥሮው ዴሞክራሲን ይጻረራል። ቬስና ፖፖቭስኪ የተባለች ጸሀፊ እንዳለችው “ዘመናዊ የዲሞክራሲ ጽንሰ ሃሳብ የተመሰረተው በጎሳ ወይም በብሄር-ብሄረሰብ ማንነት ላይ ሳይሆን በግለሰብ ነጻነትና ምርጫ ላይ ነው። አንድ ግለሰብ የፖለቲካ ነጻነቱን (የዜግነት መብቱን) የሚቀዳጀው በጎሳው አማካይነት ሳይሆን ራሱ ነጻ ሰው ሆኖ የሚፈልገውን መምረጥ ሲችል ብቻ ነው። በትክክለኛ መንፈሱ አንድ ግለሰብ የፖለቲካ ነጻነቱን የሚጎናጸፈው በጎሳው አማካይነት ሳይሆን ራስ-በቅ ዜጋ ሆኖ ነው” (Vesna Popovski, Yugoslavia: Politics, Federation, Nation, 1995) (ጥቅሱን ከእንግሊዘኛው ወደ አማርኛ የተረጎምኩት እኔው እራሴ ነኝ).

 

እስቲ የወያኔ ህገ መንግስት የሚደነግገውን ህገ መንግስታዊ ድንጋጌ ከዚህ ቀጥለን እንመልከት።

 

የወያኔ መንግስት የደነገገው ህገ መንግስት አካል የሆነው ጠንቀኛው አንቀጽ ፰ ፡ 

 

አንቀጽ ፰ የህዝብ ሉዓላዊነት ።

 

፩ – “ኢትዮጵያ ብሄሮች፤ ብሄረሰቦችና ህዝቦች የኢትዮጵያ ሉዓላዊ ስልጣን ባለቤቶች ናቸው።

 

፪ – ይህ ህገ መንግስት የሉዓላዊነታቸው መገለጫ ነው።

 

፫ – ሉዓላዊነታቸውም የሚገለጸው በዚህ ህገ መንግስት መሰረት በሚመርጧቸው ተወካዮቻቸውና በቀጥታ በሚያደርጉት ዲሞክራሲያዊ ተሳትፎ አማካይነት ይሆናል”።

 

ይህ ከላይ የተጻፈው አንቀጽ ከውጭ ሲያዩት ለኢትዮጵያ ህዝብ መብት የሚያጎናጽፍ ቢመስልም፤ መብትና ስልጣን የሚያጎናጽፈው ወያኔብሄሮች፤ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ለሚላቸው ምንነታቸውና ልዩነታችው እንኳን በቅጡ ተለየተው ላልታወቁ ስብስቦች ነው። በዚህም ምክንያትይህ አንቀጽ በማንኛውም ዲሞክራሲያዊ ስርዓት ውስጥ የሚታወቀውን የአንድን ሰው የዜግነት መብት በህገ መግንስቱ ውስጥ አይደነግግም። በዚህም ምክንያት ይህ ህገመንግስት መብት ከየሚሰጠው ብሄሮች፤ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ለሚባሉ በቋንቋ መስፈርት ለተለዩ ክልሎች ነው። በዚህ ህገ መንግስት መሰረት አንድ ግለሰብ መብቱ የሚታወቅለት የጎሳ ማንነትን መሰረት አድርገው በተሰየሙት ብሄር፤ ብሄረሰብና ህዝቦች በሚባሉት ስብስቦች በኩል ነው። አንድ ሰው መብት የሚኖረው የእነዚህ ብሄር፤ ብሄረሰብና ህዝቦች የሚባሉ ስብስቦች አባል በመሆን ነው እንጂ በዓለም ዙሪያ በሚገኙ ዲሞክራሲያዊ ሀገሮች ውስጥ እንደሚታየው በግለሰብ ሰውነቱ እንደ አንድ የኢትዮጵያ ዜጋአይደለም። ስለዚህ አንድ ኢትዮጵያዊ የሚኖረው መብት በጎሳ ማንነት ላይ ተመስርተው በታወቁት ብሄር፤ ብሄረሰቦችና ህዝቦች በሚባሉ ስብስቦች አማካይነት ብቻ ነው የሚረጋገጥለት።  አንድ ኢትዮጵያዊ መብቴ ነው ብሎ የሚለውም ነገር ተቀባይነት ያለው በእነዚህ በጎሳና በቋንቋ መስፈርት ተለይተው በታወቁት ክልሎች ውስጥ ነው እንጂ በመላው የኢትዮጵያ ክፍሎችና ክልሎች ውስጥ አይደለም። ስለዚህ ዛሬ ኢትዮጵያ በምትደዳደርበት ህገ መንግስት አንድ ኢትዮጵያዊ እንደ ዜጋ ከክልሉ ውጭ ይዞት የሚሄደው፤ በየትኛውም የኢትዮጵያ ክልል መብቴ ነው ብሎ እንዲከበርለት የሚጠይቀው መብት አልተሰጠውም። በዚህ ምክንያት አንድ የአማራ ጎሳ ተወላጅ ዛሬ ኦሮሚያ፤ ደቡብ፤ ትግራይ፤ ሱማሌም ሆነ ቢኒሻንጉል ወዘተ ተብለው በተከለሉት የኢትዮጵያ የጎሳ ክልሎች ውስጥ እንኳን ቢወለድ አንተ የዚህ አካባቢ ጎሳ ተወላጅ ስላልሆንክና አማራ ስለሆንክ ከዚህ ወጥተህ ወደ ራስህ የአማራ ክልል ሂድ ተብሎ ሊባረር ይችላል። ዶክተር ያቆብ ሃይለማርያም ዛሬ አማራውም ሆነ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ በፈለገው የኢትዮጵያ ክልል ሂዶ መኖር ይችላል ይህንንም ህገ መንግስቱ ይፈቅዳል እያለ በአሜሪካን ሬድዮ የአማርኛ ክፍል እየቀረበ ሲያስረዳ ቆይቶ አል። እውነቱ ግን ይህ አይደለም። ዶክተር ያቆብ ዛሬ በስራ ላይ የዋለው ቋንቋንና የጎሳ ማንነትን መሰረት አድርጎ የተቀረጸው ህገመንግስት መብትን ከጎሳ ማንነት ጋር በማያያዝ የአንድ ኢትዮጵያዊ መብት በጎሳ ማንነቱ ከተከለለት ክልል ውጭ እንደማይሻገር አይገልጽም። ይህን መግለጽ የጎሳን ፌዴራሊዝም አጥፊነትና አፍራሽነት ስለሚያጋልጥ የጎሳ ፌዴራሊዝም ደጋፊ የሆነው ዶክተር ያቆብ ሃይለማርያም ይህንን ጉዳይ በጭራሽ አያነሳውም። ዶክተር ያቆብ የጎሳ ፌዴራሊዝም ደጋፊ መሆኑን የሚያረጋግጥልን አንዱ ማስረጃ ከቅንጅት መፍረስ በኋላ የተመሰረተውን ህብረ-ብሄራዊ ይዘት ያለውን የአንድነት ፓርቲ በጎሳ ፌዴራሊዝም መርህ የሚያምነው የመድረክ አባል እንዲሆን የተጫወተው ከፍተኛና ቁልፍ ሚና ነው። ዶክተር ያቆብ በሚሰጣቸው የሬድዮ መግለጫዎች የዛሬው ህገመንግስት የኢትዮጵያን ዜጎች ከቦታ ቦታ ተዘዋውሮ የመኖር መብት ያረጋግጣል ሲል የዛሬው የኢትዮጵያ ህገመንግስት ዋና የማእዘን ራስ የሆነውን የአንቀጽ ስምንት ትርጉምና አንድምታ አጥቶት ወይም ዘንግቶት አይደለም። እንደሚታወቀው መድረክ የኢትዮጵያ ህዝብ ለቅንጅት በግንቦት 1997 ዓ.ም የሰጠው ሰፊ ድጋፍ ያስደነገጣቸው የጎሳ ፌዴራሊዝም አራማጆች የመሰረቱት ስብስብ ነው። የህግ ባለሙያ የሆነው ዶክተር ያቆብ ሃይለማርያም ሊነካው የማይፈልገው ጉዳይ ዛሬ አማራው ከቢኒሻንጉልም ሆነ ከጉራ ፈርዳ የሚፈናቀልበት ምክንያት ይህ በወያኔ ህገ መንግስት ውስጥ የተሰነቀረውና አንቀጽ 8 ስር የሰፈረው የጎሳ ፌዴራሊዝም ዋና መገለጫ የሆነው ድንጋጌ ነው። ኢትዮጵያ የብሄር፤ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ሀገር ነች በሚልየቡድን መብትን ከግለሰብ መብት በሚያስቀድም ህገ መንግስት ውስጥ የተሰነቀረው ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ከቦታ ቦታ ተዘዋውሮ ህይወቱን ሊመራ ይችላል የሚል አንቀጽ የአንድን ኢትዮጵያዊ መብት ሊያስጠብቅ እንደማይችልና አንድ ኢትዮጵያዊም እኔ የኢትዮጵያ ዜጋ ስለሆንኩኝ መብቴ በማናቸውም የኢትዮጵያ ክፍል ውስጥ ሊከበር ይችላል ለማለት እንደማያስቸለው ያለፉት ሃያ ሁለት ዓመታት ልምዶች አሳይተውናል። ባለፉት ሃያ ሁለት ዓመታት ኦሮሚያ ክልል በሚባለው የኢትዮጵያ ክፍል ውስጥ የሚገኙ አያት ቅድመ አያቶቻቸው እዚያ ተወልደው ያደጉ ኦሮሞ ያልሆኑ ተወላጆች በተለይም በዚህ የኦሮሚያ ክልል ተብሎ በተሰየመው ክልል ውስጥ በስፋት የሚኖሩት የአማራ ተወላጆች እናንተ መጤዎች ስለሆናችሁ የትምህርትም ሆነ የስራ እድል አይገባችሁም፤ ቅድሚያ የሚሰጠው ለኦሮሞ ተወላጆች ነው ተብለው ከማናቸውም አንድ ኢትዮጵያዊ ሊያገኝ ከሚገባው ጥቅምና መብት ተሳታፊ እንዳሆኑ ተደርገው ኖረዋል። የሌሎችም ከኦሮሞ ጎሳ ውጭ ያሉ ተወላጆች እንደዚሁ በኦሮሞ ክልል ውስጥ በኢትዮጵያዊነት የሚገባቸውን መብት ተነፍገዋል። ይህንን ጎሳን መሰረት ያደረገ አስከፊና ጎሰኛ አሰራር ኢትዮጵያ እየተመላለሰ ለረጅም ጊዜ ቆይታን ያደረገው ዶክተር ያቆብ አይቶአል፤ ድርጊቱ ከደረሰባቸውም ሰዎች ሳይሰማ አልቀረም። ለምን ግን ይህንን የኢትዮጵያ መተዳደሪያ ሆኖ ዜጎችን የአድልዎ ስርዓት ሰለባ ያደረገ ህገመንግስት ጉልህ የሆነ ጉድለትና አጥፊነት ዶከተር ያቆብ ማየት እንዳቃተውና በህገመንግስቱ መሰረት ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ወደፈለገበት የኢትዮጵያ ክፍል ሄዶ ህይወቱን ሊመራ ይችላል እያለ በአሜሪካን ድምጽ የአማርኛ ክፍል እንደሚነግረን አይገባኝም። ለዚህም ነው ከሃያ ሁለት ዓመት ጥፋት በኋላ እንኳን ዶክተር ያቆብ ይህንን የጎሳ ፌዴራሊዝምን መሰረት አድርጎ የተጻፈውን የዛሬውን ህገመንግስት ላለመንካት፤ ለላመተቸት የፈለገው። ለነገሩ ያቆብ የሚያምንበትን የጎሳ ፌዴራሊዝምን ፍልስፍና እንዴትስ አድርጎ ይቃወም? እነ ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም፤ እንደዚሁም ከአንድነት ፓርቲ ወጥተው ዛሬ የሰማያዊ ፓርቲን የመሰረቱት ወጣቶች የአንድነት ፓርቲ የጎሳን ፖለቲካ ከሚያራምደው የመድረክ ድርጅት አባል መሆን አይገባውም ብለው በመቃወም፤ የአንድነት ፓርቲም በዚህ ጉዳይ ላይ ስብሰባ አድርጎ እንዲነጋገሩበትና እንዲከራከሩበት ሲጠይቁ፤ ዛሬ በአመራር ላይ ያሉት የአንድነት ፓርቲ መሪዎችና ዶ/ር ያቆብ ኃይለማርያም ይህንን አሻፈረን ብለውና ሽንጣቸውን ገትረው የጎሰኞች ስብስብ የሆነውን መድረክ የተባለውን ዛሬ ኢትዮጵያ በምትደዳደርበት የጎሳ ፌዴራሊዝም ስርዓት ተከታይ ቡድን ተቀላቅለዋል። በኢትዮጵያ ውስጥ እየተሰራበት ያለው በቡድን መብት ላይ የተመሰረተ ህገመንግስት ዛሬም በወያኔ ይሁን ነገ እነ መድረክ በለስ ቀንቶአቸው ስልጣን ቢጨብጡ የኢትዮጵያውያንን መብት ሊያረጋግጥ አይችልም፤ ዛሬ እየሆነ እንዳለው ኢትዮጵያን በጎሳ በታትኖ ከማፍረስ የዘለለ ዓላማና ግብ የለውም። ለምን ቢሉ ይህ ህገመንግስት መብት የሚሰጠው በጎሳ ማንነት ላይ ተመስርተው በተከለሉ ክልሎች ውስጥ ላሉ ያንድ ጎሳ ተወላጆች ሲሆን እነዚህ የአንድ ጎሳ ተወላጆችም ከእነሱ ክልል ውጭ ይዘውት ወደ ሌላ ክልሎች የሚወስዱት መብት የላቸውም። አማራው የጎሳ ፖለቲካ ሰለባ የሆነበትም መሰረታዊ ምክንያት ይህ ነው። የጎሳ ፌዴራሊዝም ዛሬ በወያኔ ትግሬዎች ዘመን እየተደረገ እንዳለው የኢትዮጵያዊነት ሀገራዊ ስሜትን የሚያፈርስ፤ ጥላቻንና ጥርጣሬን የሚያስፋፋና ለእርስ በርስ እልቂት የሚጋብዝ ኢትዮጵያን እንደ ሀገር መቀጠል እንዳትችል የሚያደርግ፤ የኢትዮጵያን ህዝብ መሰረታዊ የመብትና የእኩልነት ጥያቄዎች የማይፈታ ነው። ዛሬ መንግስታዊ ስልጣን በመቆጣጠራቸው በጎሳ ፌዴራሊዝም መርህ ላይ የተመሰረተው ህገ መንግስት አተገባበር ችግር የማይፈጥርባቸው የምርጡ የትግራይ ተወላጆችና ለእንደሱ በባርነት አድረው የሚያገለግሏቸው ጥቂት የሌሎች ጎሳ ተወላጆች ብቻ ናቸው።

 አንድ በኢትዮጵያ ስላለው የጎሳ ፌዴራሊዝም ጥናት ያደረገች ሎቪስ አለን የምትባል የኖርዌይ ተወላጅ  እንዳመለከተችው የኢትዮጵያን በጎሳ ላይ የተመሰረተ ፌዴራሊዝም በዓለም ውስጥ ከሚገኙ የፌዴራል ስርዓቶች ሁሉ የተለየ የሚያደርገው እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ የዜግነት መብት የሚቀዳጀው በጎሳ ማንነቱ አማካይነት ብቻ መሆኑና በዛሬይቱ ኢትዮጵያ ዜግነት ከጎሳ አባልነት ውጭ ሊታሰብ ያለመቻሉ ሁኔታ ነው። ዛሬ አማራው ከተወለደበት፤ አድጎና ከብዶ፤ ልጆች አፍርቶ ከሚኖርበት የደቡብ፤ የኦሮሞ፤ የሶማሊ፤ የቢኒሻንጉል ወዘተ ክልሎች እንዲወጣ የተደረገው የጎሳ ፌዲራሊዝም በደነገገው ኢ-ዲሞክራሲያዊና ፋሽስታዊ የሆነ ህገ መንግስት ምክንያት ነው። ስለዚህ ስለ አማሮችም፤ ሰለ አፋሮችም፤ የጋምቤላ ተወላጆችም፤ ወዘተ መፈናቀል ሆነ በተደጋጋሚ ባለፉት ሃያ ሁሉት ዓመታት ከትግራይ ክልል ውጭ ባሉ የኢትዮጵያ ክፍሎች ለተካሂዱት በርካታ አውዳሚ የጎሳ ግጭቶችና ፍጅቶች፤ የህዝብ መፈናቀል፤ ስደትና መከራ መንስኤ ስንነጋገር ክርክራችንም ሆነ ውይይታችን ትኩረቱን ማሳረፍ ያለበት ጥላቻና ግጭትን አራጋቢ የሆነው የጎሳ ፌዴራሊዝም ኢትዮጵያን እንደ ሀገር እንድትቀጥል የሚያደርግ ነው ወይስ አይደለም? በሚለው ጥያቄ ዙሪያ መሆን አለበት የሚል አስተያየት አለኝ። ዛሬ የፖለቲካውን መድረክ ያጣበቡት በሀገርም ሆነ በውጭ ያሉት የወያኔ መንግስት ተቃዋሚዎች (የመድረክ ቡድን አባሎች፤ አዲሱና በቅርቡ ራሱን ያስተዋወቀው የኦሮሞ ዲሞክራሲያዊ ግንባር፤ በጄኔራል ከማል ገልቹ የሚመራው የኦነግ ክንፍ፤ ወዘተ) እንዲሁም ግንቦት ሰባትን የመሳሰሉት አዲሱን ኦነግንና የኦጋዴን ነጻ አውጭዎችን እያጀቡ በየመድረኩ ብቅ የሚሉት ጭምር የሚያራምዱትና የሚደግፉት የጎሳ ፌዴራሊዝም ኢትዮጵያን እንደ ሀገር እንድትቀጥል የማያስችል፤ ኢትዮጵያን የሚበትንና የእርስ በርስ ጦርነት አውድማ፤ የተፋፋመ ጅምላ የጎሳ ፍጅት የሚዳርግ መሆኑን ገደምም ጠመም ሳላደርግ መግለጽ እፈልጋለሁኝ። አስገራሚው ነገር ኢሳት የተሰኘው ሬድዮና ቲሌቪዥን የጎሳ ፌዴራሊዝም አራማጅ ለሆነው ለአዲሱ የኦሮሞ ዲሞክራሲያዊ ግንባር ወደ አንድ ጎን ያደላ ሽፋን ሲሰጥ (ኢሳት ከቀድሞው የኢሰፓ ካድሬ ዛሬ ደግሞ የአዲሱ የኦሮሞ ዲሞክራሲያዊ ግንባር አንዱ መሪ ከሆነው ከዶክተር በያን ሁሴን ኦሶባ፤ ጋር ያደረገውን ሰፊና ተከታታይ ቃለመጠይቅ ያሰተውሏል) እንደ “ነጻ የመገናኛ ብዙሃን ተቋም” ይህንን አዲሱ የኦነግ ክፍል ያነገበውንና በወያኔ የሃያ ሁለት ዓመታት አስተዳደር ስራ ላይ ውሎ ኢትዮጵያን እንደ ሀገር እያፈረሰ ያለውን የጎሳ ፌዴራሊዝም የሚቃወም አመለካከት ለማስተናግድ ግን ፈቃደኛ አልሆነም። በዚህም ሳቢያ የእሳት ባለቤት የሆነው የግንቦት ሰባት ድርጀት አሻራ ከምንጊዜውም በላይ ጉልህ ሆኖአል።

 ከላይ እንደ ገለጽነው  ብሄር፤ ብሄረሰቦችና ህዝቦች የሚባሉትን የወል ስብስቦችን መሰረት ያደረገው የዛሬው የኢትዮጵያ ህገ መንግስት መብት የሚሰጠው ለእነዚህ ስብስቦች እንጂ ለእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ዜጋ አይደለም። በማናቸውም ዲሞክራሲያዊ ሀገር እንደሚታየው ሉዓላዊነት የሚሰርጸው ነጻ ከሆነው እያንዳንዱ ዜጋ ነጻ ምርጫ እንጂ ብሄር፤ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ከሚባሉ የማይጨበጡ ስብስቦች አይደለም። በዲሞክራቲክ መንግስታዊ ስርዓቶች ህገ መንግስት ውስጥ ተገልጾ የምናነበው ሉአላዊነት የሚሰርጸው ከእያንዳንዱ ግለሰብ ነጻ ፈቃድ ሲሆን እያንዳንዱ ነጻ ያንድ ሀገር ዜጋ ድጋፉን የሚሰጣቸው የህዝብ ተወካዮች ፓርላማ ገብተው በዚያ በተሰጣቸው የእያንዳንዱ ዜጋ ህዝባዊ ውክልና መሰረት ዲሞክራሲያዊ የህዝብ መንግስት ያቋቁማሉ። ይህም በእያንዳንዱ ዜጋ ነጻ ፈቃድ ላይ ተመስርቶ የተቋቋመ መንግስት ተጠሪነቱ ብሄር፤ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ለሚባሉ የማይዳሰሱና የማይጨበጡ የወል ስብስቦች ሳይሆን ለእያንዳንዱ የመምረጥ መብት ላላው ነጻ ዜጋ ይሆናል። በዚህ ዓይነት የአንድ ሀገር ሉዓላዊነት የሚሰርጸው ብሄር፤ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ከሚባሉ የወል ስብስቦች ሳይሆን ከእያንዳንዱ የኢትዮጵያ ዜጋ ነጻ ፈቃድ ይሆናል። የአንድ ሀገር ዜጎች በዚህ ዓይነት በየግላቸው በፈቃዳቸው በሚሰጡት ህዝባዊ ውክልና የሚመሰረት መንግስት ተጠሪነቱ ለዚያ ለመረጠው ህዝብ ስለሚሆን ይህ ተጠሪነቱ ለህዝብ የሆነ መንግስት የመረጠውን፤ በስሙም መንግስት እንዲመሰርት የወከለውን ህዝብ በደንብ ሳያገለግል ሲቀር ይህ ነጻ ህዝብ በምርጫ ድምጹን በመንፈግና ውክልናውን በማንሳት ይህንን መንግስት በሌላ የተሻለ መንግስት ሊተካ ይችላል። የዲሞክራቲክ ሀገሮች ለህዝቦቻቸው ልማትና እድገትን፤ ሰላምና ደህንነትን፤ የተረጋጋ ማህበረሰባዊና ፖለቲካዊ ህይወትን ያረጋገጡት በዚህ ዓይነት ከእያንዳንዱ ነጻ የሆነ ዜጋ ፈቃድና ምርጫ በተቋቋሙ መንግስታት እንጂ ስልጣን-ወዳድ ልሂቃን በብሄር፤ ብሄረሰቦችና ህዝቦች በሚባሉ የወል ስብስቦች ስም የዚህ ወይም የዚያ ጎሳ ወኪል ነን ብለው በህዝብ ላይ በሚጭኑት፤ ከፋፋይና የማያባራ የጥላቻና የእልቂት መንሥኤ ሊሆን በሚችል የጎሳ ፌዴራሊዝም ስርዓት አይደለም። በዚህ ጸሃፊ እምነት ተማርኩ ነኝ ባዩ የኢትዮጵያ ማህበረሰብ ክፍል ላለፉት ሃምሳና ስልሳ ዓመታት ጥናትና ምርምር ላይ ያልተመሰረቱ፤ የኢትዮጵያን ህዝብ መሰረታዊ ችግሮች ያልቃኙ ዝም ብለው በመፈክር ደረጃ የሚገፉ ሃሳቦችን (የብሄረሰብ መብት፤ የመደብ ትግል፤ ወዘተ) በኢትዮጵያ ህብረተሰብ ላይ በመጫን የኢትዮጵያን ህብረተሰብ እንደ ቤተ-ሙከራ (ላቦራቶሪ) የአውዳሚ ሃሳቦችና ድርጊቶች ሰለባ አድርጎአል። ይህ የዚህ ጽሁፍ ጸሃፊም በለጋ የወጣትነት እድሜው ለሶስት ዓመታት ኢህአፓን በጀሌነት ተቀላቅሎ ለዚህ በእንጭጭ አይምሮ ለተቀፈቀፈ አፍራሽና አውዳሚ ሃሳብ ተግባራዊነት የበኩሉን የጥፋት አስተዋጽዖ አድርጐአል። በዚህ ትውልዳችን በፈጸመው ጥፋት ከመኩራራት ይልቅ በተደጋጋሚ በአደባባይ ይቅርታም ጠይቆአል። ዳሩ ግን ይህ ያልተመረመሩና ጥናት ያልተደረገባቸውን ጎጂ የሆኑ የፖለቲካ ሃሳቦችን በማህበረሰባችን ላይ የመጫኑ አዝማሚያ ዛሬም ቀጥሎአል።፡ ቢያንስ በውጭ ሀገር በነጻው ዓለም የምንኖረው ኢትዮጵያውያን እንዲሁ በጀሌነት የተለያዩ የፖለቲካ ድርጅቶች የሚያራግቧቸውን የፖለቲካ መፈክሮች ተቀባይና እንደ ገደል ማሚቶ አስተጋቢ ደጋፊዎች ከመሆናችን በፊት የጎሳ ፌዴራሊዝም የሚባለው የፖለቲካ አስተሳሰብ ለኢትዮጵያ ሀገራዊ ፋይዳው ምን ይመስላል?፤ የጎሳ ፌዴራሊዝም አራማጅ የነበሩ የቀድሞዋን ዩጎዝላቪያና የሶቬዬት ህብረት የመሳሰሉት ሀገሮች መጨረሻ ምን ሆነ? ብለን መጠየቅ ይኖርብናል። በጎሳ ማንነት ላይ የተደራጀ አግላይ ፖለቲካ አግላይነትን ከሚጻረረው የዲሞክራሲ ጽንሰ-ሃሳብ ጋር ያለውን ርቀት መገንዘብ ያስፈልጋል። የጎሳ ፌዴራሊዝም ከዲሞክራሲ ጋር ምንም ግኑኝነት የለውም። እኔ የጎሳ ፌዴራሊዝም የዲሞክራሲም መገለጫ አይደለም ብዬ እከራከራለሁኝ እሞግታልሁኝ። እስቲ በዚህ በጎሳ ፌዴራሊዝም ዙሪያ የዚህ አራማጅ የሆኑት በርካታ በኢትዮጵያም ሆነ (የመድረክ አባሎችን ያጠቀልላል) ከኢትዮጵያ ውጭ ያሉ በጎሳ ማንነት ላይ በተመሰረተ የፖለቲካ ስርዓት የሚያምኑ ወገኞች በአደባባይ ክርክር ያድርጉበት። የጎሳ ፌዴራሊዝም እኔ የኢትዮጵያ ህዝብ ብዬ ለምጠራው፤ የጎሳ ፌዴራሊዝም ደጋፊዎች የኢትዮጵያ ህዝቦች ብለው ለሚጠሯቸው ኢትዮጵያውያን ለምን እንደሚበጅ ወይም እንደማይበጅ ቢያንስ ከሃያ ሁሉት ዓመታት የጋራ ጥፋት በኋላ ውይይትና ክርክር ሊደረግበት ይገባል ብዬ እሞግታለሁኝ፤ እከራከራለሁኝ። ይህንንም ክርክር እነዚህ የጎሳ ፌዴራሊዝም አራማጆች እና ደጋፊዎች በብልጠት እንደሚያደርጉት ወደፊት የኢትዮጵያ ህዝብ የስልጣን ባለቤት ሲሆን ይወስነዋል የሚለውን ማታለያቸውን ትተው ዛሬ ገና እነሱ ወደ ስልጣን ሳይወጡና የኢትዮጵያን ህዝብ እንደ ወያኔ ትግሬዎች የጭቆና ቀንበር ሳይጭኑበት በአደባባይ ሃሳባቸውን ህዝብ በተሰበሰበበት መድረክ ወጥተው ለከራከሩበት ይገባል። ይህ በየመድረኩ ለፖለቲካ ተቃዋሚዎች የሚያጨበጭበው በስደትም ሆነ በሀገር ቤት የሚኖር ህዝብ ቢያንስ አማራጭ እንሰጥሃለን ብለው ድጋፉን የሚሹትን ተቃዋሚ የፖለቲካ ቡድኖች ስለ ትልማቸውና አንግበውት እንታገልለታለን ስለሚሉት የጎሳ ፌዴራሊዝምን መሰል አጀንዳ ጥያቄዎችን መጠየቅ አለበት። የጠላቴ ጠላት ወዳጄ ነው በሚል የሞኞች ብሂል ወያኔን የተቃወመ ሁሉ ወዳጄ ነው አማራጭ ይሆነኛል ማለትን ማቆም አለበት። የጎሳ ፌዴራሊዝም  የአንድ የባለ-ብዙ ጎሳዎችና እምነቶች ባለቤት ለሆነች ኢትዮጵያን ለመሰለች ሀገር አይረባትም ብዬ በጽኑ ከሚያያምኑት ሰዎች መካከል ነኝ። በዚህም ጉዳይ የመድረክን አባሎች ከመሳሰሉት የጎሳ ፌዴራሊዝምን ጠቃሚነት ከሚሰብኩ ወገኖች ጋር በሃሳብ በአደባባይ በአካልም ሆነ በጽሁፍ ወጥተን፤ ጸሃይ እየሞቀን፤ ሰው እያያን እንድንከራከርበት በትህትና እጠይቃለሁኝ።

 

በዚህ በጎሳ ፌዴራሊዝም ጉዳይ ላይ ህዝብ የተሳተፈበት ግልጽ ክርክር በአደባባይ እንዲካሄድ ቢያንስ በነጻው የምእራቡ ዓለም የሚኖረውና በየጊዜው ስብሰባ እየተጠራ ስለሀገሩ ጉዳይ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲ ነን የሚሉ ወገኖችን የሚያዳምጠውና የሚደግፈው ኢትዮጵያዊ መጠየቅ ይኖርበታል። ይህ ግልጽ የሆነ ክርክር እንዳይካሄድ ባገር ቤትም ሆነ በውጭው ሀገር አልተቻለም። ያ የኢትዮጵያ ተማሪዎችና የግራው እንቅስቃሴ ውላጅ የሆነው ጸረ-ምሁራዊ ልማድ ዛሬም ድረስ ቀጥሏል። የተለያዩ አመለካከት ያላቸውን ወገኖች ባንድ መድረክ ላይ አቅርቦ ሃሳባቸውን ለህዝብ እንዲያቀርቡ ማድረግ እስካሁን ተቀባይነትን አላገኝም። ከዚያ ይልቅ በደጋፊዎች የታጀበ፤ የተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅት መሪዎች ነን የሚሉ ወገኞች የራሳቸውን ሀሳብ (በሞኖሎግ መልክ) ብቻ ተናግረው የሚሄዱበት፤ የእነሱን ሃሳብ የሚቃወሙ ድምጾች በስልት የሚታፈኑበት ከዚያው ከግራው ፖለቲካ የቀጠለ አሰራር ቀጥሏል። በዚህ በምእራቡ ዓለም በስደት ያለነው ኢትዮጵያውያን እንኩዋን በተቃዋሚዎች ስብሰባ ላይ እየተገኘን ያንድን ወገን ድምጽ እየሰማን ከማጨብጨብ በስተቀር የፖለቲካ ድርጅቶች ለሀገርና ለህዝብ ይጠቅማሉ ብለው የሚያራምዿቸው ሃሳቦች በአደባባይ ክርክር እንዲደረግባቸው ተጽዕኖ ማድረግ አልቻልንም። በቅርቡ የቀድሞው የወያኔ ካድሬ፤ የዛሬው የግንቦት ሰባት ዋና ጸሀፊ አንዳርጋቸው ጽጌ ዋሽንግተን ላይ ሆኖ ካለአንዳች ሃፍረትና ይሉኝታ የኢትዮጵያ የነጻነት ትግል በኤርትራ ህዝብና መንግስት እየተረዳ ኢትዮጵያን ነጻ ሊያወጣ እንደሚችል ተረት ሲነግረንና ሊያሳምነን ሲሞክር እዚያ ተሰብስበው የሚያዳምጡትና የሚያጨበጭቡለት ወገኖች ክቅርብ ታሪካችን ምን ተማሩ? ብዬ እንድጠይቅ አድርጎኛል። አንዳርጋቸው እንደማናቸውም ዓይነት ህሊና እንደሌለው ሳይካትሪስቶች ሳይኮፓቲክ ፐርሶናሊቲ እንደምንለው መዋሸት፤ መቅጠፍ ለህሊናው አይከብደውም፤ ህሊናውን አይቆረቁረውም። አሳዛኙ ነገር የኢትዮጵያ ፖለቲካ ትላንት መንግስቱ ኃይለማርያምን፤ መለስ ዜናዊን ዛሬ ደግሞ አንዳርጋቸውን የመሳሰሉ ሳይኮፓቲክ (ህሊናቢስ የሆነ ተክለሰውነት ያለው፤ መቅጠፍ መዋሸት የማይሰቀጥጠው፤ ሰው ማለት ነው) ግለሰቦች መፈነጫነት ምቹ ሜዳ መሆኑ ነው። ይህ ኢትዮጵያውያን ልናጠናው የሚገባን አሳሳቢ ብሄራዊ ችግር ነው። የዛሬ ሃያ ሁለት ዓመት ከወያኔ ትግሬዎች ጋር ሆኖ ኢትዮጵያን በመቆጣጠር እንደ ማናቸውም የወራሪ ጦር የኢትዮጵያን ግማሽ ሚሊዮን ጦር ከነቤተሰቡ የበተነውን፤ ትጥቃቸውን ፈተው እጃቸውን በሰላም የሰጡ አራት ሽህ የኢትዮጵያ መኮንኖችን ካለአንዳች ርህራሄ የፈጀውን ሻቢያን፤ የወርቅ ጥርስ ሳይቀር ነቅሎ ከሁለት መቶ ሺህ በላይ ቁጥር ያላቸውን ኢትዮጵያውያንን ከኤርትራ ያባረረውን ሻቢያን፤ እስከ ባድሜ ጦርነት ድረስ ከወያኔ ትግሬዎች መንግስት ጋር ሆኖ የኢትዮጵያን ሃብት እንደ ጠላት ንብረት ሲዘርፍና ወደ ኤርትራ ሲያሸሽ የነበረውን ሻቢያን፤ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ አውታሮችን ተቆጣጥሮ ሲመዘብር የነበረውን ሻቢያን፤ በቅንጅት ድል ማግስት ኬንያ (ናይሮቢ) እና ሆላንድ (ዩትሬክት ከተማ ላይ) ከእነ ኦነግ ጋር በመመሳጠር አላያንስ ፎር ዲሞክራሲ (ኤፍዲ) በሚል ስም የኢትዮጵያን ህዝብ የምርጫ ውጤት ለመንጠቅ የሞከረውን ሻቢያን እኩይ ድርጊት የኢትዮጵያ ህዝብ ፈጽሞ አይረሳም። መርሳትም የለበትም። ትላንትም ዛሬም የኢትዮጵያን ህዝብ ጠላቶች በጎሳ እያደራጀ የሚያሰማራው ሻቢያ፤ ዛሬ በወያኔ ግፍና ጎሰኛ አገዛዝ ተማረው ወደ ኤርትራ የሚገቡትን የኢትዮጵያ ወታደሮች በጎሳ እየለያየ (አማራ፤ ኦሮሞ፤ አፋር፤ ሶማሊ፤ ሲዳማ ወዘተ እያለ) የሚከፋፍለው ሻቢያ ለኢትዯጵያ በጎ ነገር ያስባል ብለው የግንቦት ሰባት መሪ ካድሬዎች ሊያሞኙን ሲሞክሩ ምን ያህል የኢትዮጵያውያንን የማሰብ ችሎታ ዝቅ አድርገው እንዳዩት ያሳየኛል። የግንቦት ሰባት መሪ ካድሬዎች (አንዳርጋቸውም ሆነ ብርሃኑ ነጋ፤ ወዘተ) እነሱ በማይቆጣጠሯቸው የህዝብ መድረክ ላይ ቀርበው ሌሎች የእነሱን ሃሳብ ከሚቃወሙ ወገኖች ጋር መድረክ በመጋራት የያዙትን አቋም ለማቅረብ ድፍረቱም ሆነ ችሎታው እንደሌላቸው አውቃለሁኝ። ነገር ግን ዛሬ በሞኖፓል በሚቆጣጠሩት የኢሳት ሬድዮና ቴሌቭዥን አማካይነት በአእምሮ ችሎታቸው ዝቅ ያሉ ወገኖችን ሊያሞኙ ይችሉ ይሆናል። እንኳን ሻቢያ ይቅርና ኤርትራ የሚባለውን የጣሊያን ቅኝ ገዢዎች የፈጠሩትን የባርነት መገለጫ የሆነውን አዲስ ጸረ-ኢትዮጵያ ማንነት የተላበሱ ወገኖች ምንጊዜም ለኢትዮጵያ በጎ እንደማያስቡና እንደማይተኙላት አንባቢ ልብ እንዲል ይህ ጸሀፊ አበክሮ ያሳስባል። አንድ ስለ ኤርትራ ብሄረተኞች ሰፊ ጥናት ያደረገ ኢትዮጵያዊ የታሪክ ምሁር ባንድ ወቅት እንዳለው “ውሃ ጠማኝ ተብሎ መርዝ አይጠጣም”። እንደዚሁም ዛሬ በወያኔ ትግሬዎች ጎሰኛ ስርዓት የተበሳጨ የጠላቴ ጠላት በሚል የሞኝ ብሂል ምንጊዜም ጠላትነቱን ለማይተወው የሻቢያ ኤርትራ ልቡን ሊሰጥ አይገባም። ወደፊት ይህንን የኤርትራን ማንነትና ጉዳይ አስመልክቶ ሌላ መጣጥፍ ለማቅረብ አስባለሁኝ። በዚህ ጽሁፌ ውስጥ ስማቸው የተጠቀሱት ግለሰቦች ወይም የድርጅት ወኪሎች፤ መሪዎች ያነሳኋቸውን የተቃውሞ ነጥቦች አስመልክቶ የሚኖራቸውን አስተያየት ለማስተናገድ፤ አስፈላጊም ከሆነ በማንኛውም መድረክ ላይ ቀርቤ ለመከራከር ዝግጁ መሆኔን በትህትና አሳውቃለሁኝ።

 

* የዚህ ጽሁፍ ጸሀፊ አሰፋ ነጋሽ በሆላንድ የሚኖር ኢትዮጵያዊ ስደተኛ ሲሆን በዚሁ በተሰደደበት ሀገር በተማረው የህክምና ሙያ የአይምሮ ሀኪም (ሳይካትሪስት ሆኖ እየሰራ ይገኛል)። አንባቢያን ይህን ጽሁፍ አስመልክቶ ለሚሰጡአቸው አስተያየቶችም ሆነ ትችቶች ጸሀፊውን በሚከተለው የኢሜይል አድራሻ ማግኘት ይችላሉ። ——–›  Debesso@gmail.com 

Check Also

ሰሎሞን ካሳ ማነው? Who is Solomon Kassa?

አንከር ሚዲያ እንደዘገበው .. ለማታውቁት ሰለሞን ካሳ ይባላል ., ወንጀለኛው የሆነው ይህ ሰው የህዝብ ድምፅ …

የአድዋ በአል በለንደን ከተማ በደማቅ ተከበረ

Multi threaded Redundant Dedicated Server in USA and in Europe.