Breaking News
Home / Amharic / የዐቢይ እና የጃዋር ግብግብ – በፍቃዱ ኃይሉ

የዐቢይ እና የጃዋር ግብግብ – በፍቃዱ ኃይሉ

አክቲቪስት ጃዋር መሐመድ እና ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ደጋግመው የሚጠሩ ሥሞች ናቸው። ሁለቱም የየራሳቸው የኀይል ምንጭ እና የቅቡልነት አድማስ ያላቸው ጉልበተኞች ናቸው።

አክቲቪስት ጃዋር መሐመድ እና ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ደጋግመው የሚጠሩ ሥሞች ናቸው። ሁለቱም የየራሳቸው የኀይል ምንጭ እና የቅቡልነት አድማስ ያላቸው ጉልበተኞች ናቸው። ዐቢይ አሕመድ ከገዢው ፓርቲ ጉያ ጃዋር ጉልሕ አሻራ ባሳረፈበት ተቃውሞ ተረማምደው ጠቅላይ ሚኒስትርነትን የተቆናጠጡ መሪ ናቸው። ጃዋር መሐመድ ደግሞ ዐቢይ አሕመድ በከፈቱት የፖለቲካ ምኅዳር ዋስትና ተማምኖ አገር ቤት የገባ ፖለቲከኛ ነው። ሁለቱም ሳያስተውሉት የማይስምሙ ነገር ግን ሊነጣጠሉ የማይችሉ ተቀናቃኝ የፖለቲካ ኀይሎች ሆነዋል።

መጀመሪያ እንዲህ ነበር…

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የኦሕዴድ የድርጅት ጉዳይ ኀላፊ በነበሩበት ወቅት አክቲቪስት ጃዋር የሚወዳቸው ዓይነት ሰው አልነበሩም። እንዲያውም ክፉኛ ሲያብጠለጥላቸው እና ‘ክብረ ነክ’ ሊባሉ የሚችሉ ስድቦችን ሲያሳርፍባቸው የሚያሳይ ቪዲዮ አለ። ከትንሽ ጊዜ በኋላ ዐቢይ አሕመድ የኦሕዴድ ከዚያም የኢሕአዴግ ሊቀ መንበር ሆነው ጠቅላይ ሚኒስትር ሲሆኑ፥ የጃዋር መሐመድም ትችት በመጠኑ ቀነሰ። ሁለቱ ፖለቲከኞች ለመጨረሻ ጊዜ ፍቅር በፍቅር ሆነው የታዩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ አሜሪካ የሚገኙ ኢትዮጵያውያንን በጎበኙበት ወቅት ነበር። እውነቱን ለመናገር ጠቅላይ ሚኒስትሩ የአሜሪካ ዳያስፖራዎችን ሲጎበኙ ሁለት የዳያስፖራ መንግሥታትን ጎብኝተው የተመለሱ ነበር የሚመስለው – ታማኝ በየነን በዋሽንግተን ዲሲ እና ጃዋር መሐመድን በሚኒያፖሊስ።

ጃዋር መሐመድ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ ጓዛቸውን ጠቅልለው ከመጡ ጉምቱ ዳያስፖራዎች መካከል ግንባር ቀደሙ ነው። የኦሮሞ ሚዲያ ኔትዎርክ (ኦኤምኤን) ቴሌቪዥን ሥራ አስፈፃሚ እንደመሆኑ መጠን፣ እንዲሁም በፌስቡክ ከፍተኛ ተከታይ ያለው እና በኦሮሞ ወጣቶች ዘንድ ተደማጭነት ያለው በመሆኑ ለዐቢይ አሕመድ ፖለቲካ በረከት ብቻ ሳይሆን መርገምት እንደሚሆንባቸው ቀድሞም የሚገመት ነበር። ጃዋር የሚዲያ ተፅዕኖውን ለማስፋት በመንቀሳቀስ ከቴሌቪዥን በተጨማሪ በመጽሔት እና በኤፍ ኤም ሬዲዮም ሐሳቦቹን ለማንሸራሸሪያ መድረክ ፈጥሯል።

 

መጀመሪያ አካባቢ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ተቀባይነት እጅግ ከፍተኛ የነበረ በመሆኑ የጃዋር ተፅዕኖ በከፊል ተዳክሞ ነበር። ሆኖም፣ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ማኒፌስቶ ሊባል የሚችለውን “መደመር” ካልኩሌተር የሠራንላቸው እኛ ነን ከሚለው አንስቶ በአገሪቷ ውስጥ የቄሮ እና የእርሳቸው መንግሥት አለ የሚለውን የመሣሠሉ አወዛጋቢ ንግግሮችን ሲናገር ሰንብቷል። ከጊዜ ወደ ጊዜ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ዝና እየተዳከመ ሲመጣ የጃዋር መሐመድ ዝና እና ተፅዕኖ እንደገና እየገነነ መጣ።

ልዩነት አንድ፦ ‘ሰቦኑማ’

በርካታ የኦሮሞ ብሔርተኞች በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ላይ ያላቸውን ቅሬታ የሚገልጹት “‘ሰቦኑማ’ የላቸውም” በማለት ነው። ‘ሰቦኑማ’ ወደ አማርኛ ሲመለስ ብሔርተኝነት ማለት ነው። ይኸው ጉዳይ ገና ከመጀመሪያው በኦኤምኤን ቴሌቪዥን የክርክር ርዕሰ ጉዳይ ሆኖ ነበር። በርግጥም ብዙዎች እንደሚያስተውሉት ዐቢይ አሕመድ ከኦሮሞ ብሔርተኝነት ይልቅ የኢትዮጵያ ብሔርተኝነት ባሕርይ ነው ያላቸው።

ጃዋር መሐመድ ወደ ኢትዮጵያ ከተመለሰ በኋላ የተመለከተው የቅቡልነት አድማሱ በኦሮምያ መወሰኑ እና የጠቅላይ ሚኒስትሩ ‘ሰቦኑማ’ ወደ ኢትዮጵያ ብሔርተኝነት ማዝመሙ ትኩረቱን ወደ ኦሮሚያ ክልል አስተዳደር እንዲያዞር አድርጎታል። ስለሆነም ፌዴራሉ መንግሥት ወይም የፌዴራሉ መቀመጫ የሆነችው ራስ ገዝ ከተማ – አዲስ አበባ – ላይ ተፅዕኖ ለማድረግ ሲፈልግ የኦሮሚያ መንግሥትን ማስጨነቅን እንደስልት መጠቀም ጀመረ። በዚህም የተነሳ የኦሮሚያ አመራሮች ወደዱትም ጠሉትም እሱን ማስከፋት እንደማያዋጣቸው በመገመት “ጃዋር ምን አለ” እያሉ የሚወስኑ እና የወሰኑትንም የሚሽሩ አመራሮች ሆነዋል። ጃዋር ዐቢይ አሕመድን የሚገዳደራቸው በቀጥታ ሳይሆን በተዘዋዋሪ ነው።

ልዩነት ሁለት፦ ውሕደት እና ግንባር

ዐቢይ እና ጃዋር የቆየው ልዩነታቸው እንዳለ ሆኖ አሁን የተባባሰው ቅራኔያቸው የጠቅላይ ሚኒስትሩ የፓርቲ ውሕደት ላይ ጠንካራ ትችት ባገኘው መንገድ ሁሉ መሰንዘሩን በመቀጠሉ ነው። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ፓርቲያቸውን አንድ ላይ ለማስቀጠል በሚያደርጉት የሞት ሽረት ትግል ውስጥ የጃዋር ተቺ ሆኖ መምጣት ከኦሮሞ ዴሞክራቲክ ፓርቲ (ኦዲፒ) አባላት ብዙዎቹን ሊያሳጣቸው እንደሚችል አይጠፋቸውም። በሰሞኑ የፓርላማ ምልልሳቸው ወቅትም እሱን ለማሳጣት በሚመስል መልኩ የውጭ አገር ፓስፖርት እና ሚዲያ የያዙ ሰዎች ላይ ከፍተኛ ትችት ያሳረፉት በዚህ ብስጭት ይመስልባቸዋል።

የኢሕአዴግ ውሕደት ጉዳይ የመጀመሪያ ተቃዋሚ ሕወሓት ቢሆንም፥ ጃዋር መሐመድ እዚህ ላይ መደረቡ ለውሕደቱ ከፍተኛ ፈተና ነው። ጃዋር መሐመድ የኢሕአዴግ አጋር ፓርቲ ይባሉ የነበሩትን ያካተተ ግንባር ሆኖ መቀጠል እንዳለበት እና ግንባሩ ከዚህ በፊት “በእኩልነት መርሕ” ይመራበት የነበረው ምክር ቤቱ በተመጣጣኝ ኮታ (ሕወሓት በዚህ አይስማማም) መርሕ አባል ድርጅቶቹ በሚወክሉት ክልል ነዋሪ ብዛት እንዲወሰን ጠይቋል። ሌላው አማራጭ አደገኛ ነው ብሏል። በውሕዱ ፓርቲ ግለሰቦች ራሳቸውን እንጂ ብሔራቸውን ወክለው ስለማይገቡ የቡድን መብት አደጋ ላይ እንደሚወድቅ ስጋቱን ገልጿል።

ዐቢይ አሕመድ በበኩላቸው ስጋቱ ከንቱ መሆኑን መጽሐፋቸውን ባስመረቁበት ወቅት ተናግረዋል። አሁን በአንድ ክልል ውስጥ ገዢው ፓርቲ አንድ ቢሆንም፥ በሥማቸው ፓርቲ ያልተሰየመላቸው የሌላ ብሔር ቡድኖች አልተጨፈለቁም የሚል መከራከሪያ ሰንዝረዋል። የሆነ ሆኖ ጃዋር መሐመድ “ለምርጫ ለመወዳደር እያሰብኩ ነው” ማለቱ ደግሞ ነገሩን የበለጠ ያከርረዋል። ምክንያቱም ለምርጫ የሚወዳደረው አማራጭ ፓርቲ ይዞ በመምጣት ሊሆን ይችላል።

ልዩነት ሦስት፦ ወጣቶች እና የመንግሥት መዋቅር

ጃዋር መሐመድ “ውጡ” የሚለውን ቃል ባይጠቀም እንኳን እንዲወጡ ሲፈልግ የልቡን አውቀው “ሆ” ብለው የሚወጡ ወጣቶች አሉት። ጠቅላይ ሚኒስትር ደግሞ የአገሪቱ ጦር ሠራዊት የበላይ አዛዥ ናቸው፤ የክልል መንግሥታቱ አብረዋቸው ቢሠሩም ባይሠሩም የመንግሥታዊ መዋቅር የቁጥጥር የበላይነት አላቸው። ሁለቱም ማን የበላይ እንደሆነ ማሳየት ይፈልጋሉ። ሁለቱም አንዱን የማስገበር ፖለቲካዊ ጫወታ ይጫወታሉ።

ባለፉት ሦስት ቀናት በአዲስ አበባ እና በኦሮሚያ የተመለከትናቸው አመፆች እና ተቃውሞዎችን እንደ ነጠላ ክስተት ማየት የዋህነት ነው። እነዚህ ከላይ የጠቀስናቸው ልዩነቶች እና ፉክክሮች የፈጠሯቸው ቀውሶች ናቸው። የዐቢይ አሕመድ መንግሥት ለጃዋር የመደበለትን ጥበቃ (ያውም በሌሊት) ሊያነሳ ሲሞክር ጃዋር መደንገጡ አይቀርም። ቢሆንም ግን የራሱን ኀይል የማሳያ አጋጣሚ አድርጎ መውሰዱ ከአንድ የፖለቲካ ሰው የሚጠበቅ ነው። የሚያሳዝነው በሁለቱ ኀያላን መካከል በሚደረገው ግብግብ ተጎጂዎች ምስኪን ደጋፊዎቻቸው ናቸው። እስከ ትላንት ድረስ በደረሱን መረጃዎች ብቻ የ16 ሰዎች ነፍስ ተቀጥፏል።

Check Also

አማራና ትግሬ ተስማሙና ኦሮሙማን መክቱ። – ሞጣ ቀራንዮ

https://fb.watch/f-ipLpwPrZ/ Related Posts:አማራና ኦሮሞ አትጣሉ። ተዋደዱ !አማራና ትግሬ ወደ አዲስ አበባ እንዳይገቡ የኦሮሞ ክልል አስተዳደር …

ማስጠንቀቂያ ለከንቲባ አዳነች እቤቤ!

Related Posts:የጃዋር ሞሃመድ የዜግነት አወዛጋቢ ጉዳይ. ጃዋር ማስጠንቀቂያ ተሰጠው !

Multi threaded Redundant Dedicated Server in USA and in Europe.