Breaking News
Home / Amharic / የክልል መለያ ከተሽከርካሪዎች ሰሌዳ ላይ እንዲነሳ የሚያደርግ ረቂቅ አዋጅ ለፓርላማ ተመራ::

የክልል መለያ ከተሽከርካሪዎች ሰሌዳ ላይ እንዲነሳ የሚያደርግ ረቂቅ አዋጅ ለፓርላማ ተመራ::

በ97 ምርጫ ምክንያት ተጠሪነታቸው ለፌዴራል የተደረጉት የትራንስፖርት ቢሮዎች ለከተሞቹ ይመለሳሉ

የሚኒስትሮች ምክር ቤት ሐሙስ ጥር 12 ቀን 2014 ዓ.ም. ባካሄደው አራተኛ መደበኛ ስብሰባው፣ የክልል መለያ በተሽከርካሪዎች ሰሌዳ ላይ እንዲነሳ የሚያደርግ ረቂቅ አዋጅ ለፓርላማ መራ፡፡

ምክር ቤቱ የተወያየበት ረቂቅ አዋጅ ከተሽከርካሪ መለያ፣ መመርመርያና መመዝገቢያ አዋጅ ጋር በአባሪነት ተያይዞ ያለውን ሰንጠረዥ ይሽራል፡፡

በዚህ ረቂቅ አዋጅ የሚሻረው ሰንጠረዥ የተሽከርካሪ መለያ ቁጥር ሰሌዳ ዓይነቶችና ምልክቶችን በዝርዝር የደነገገ ሲሆን፣ እንደ ተሸከርካሪዎቹ አገልግሎት የሚኖራቸውን ቀለምና መለያ አስቀምጧል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ሰንጠረዡ እንደ አአ፣ ኦሮ፣ አማ፣ ደሕ እና ሌሎች አሥራ ሁለት የክልልና ከተማ አስተዳደሮችን የሚወክሉ ምህፃረ ቃሎችን ዘርዝሮ፣ ተሽከርካሪዎቹ እንደ ተመዘገቡበት ክልል ወይም የከተማ አስተዳደር ሰሌዳቸው እንዲሠፍር ያዛል፡፡

የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር አሁን ያዘጋጀው የመንገድ ትራንስፖርት አዋጅ፣ ይኼንን አሠራር በማስቀረት ወጥነት ያለው ብሔራዊ የተሽከርካሪ ሰሌዳ አሠራር ለመዘርጋት አልሟል፡፡ በሚኒስቴሩ የሕግ አማካሪ አቶ አበጀ ማሞ ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ ለተወካዮች ምክር ቤት የተመራው ረቂቅ አዋጅ ከፀደቀ በኋላ የክልል መለያ የያዙ የተሽከርካሪ ሰሌዳዎች ተግባራዊ የሚሆኑት አዲስ ብሔራዊ ሰሌዳ ይፋ እስኪደረግ ብቻ ነው፡፡

እንደ አማካሪው ገለጻ፣ ኢትዮጵያ ባለፈው ዓመት የፈረመችው እ.ኤ.አ. የ1968 ‹‹የቬዬና የመንገድ ትራፊክ ኮንቬንሽን››፣ ፈራሚ አገሮች ብሔራዊ ደረጃን የያዘ መለያ በአገሮች ውስጥ ለሚገኙ ተሽከርካሪዎች እንዲሰጡ ያዛል፡፡ ይሁንና የተሽከርካሪ መለያ፣ መመርመርያና መመዝገቢያ አዋጅ ላይ የተቀመጠው አሠራር ክልሎች የየራሳቸውን መለያ የያዘ ሰሌዳ እንዲሰጡ እንጂ፣ ወጥነት ያለው አገር አቀፍ የተሽከርካሪ ሰሌዳ ተግባራዊ እንዲደረግ አይፈቅድም፡፡ ‹‹ተሽከርካሪ ዓለም አቀፍ ቁስ ነው፣ አንድ መኪና ከዚህ ተነስቶ ኬንያም ሆነ ሱዳን ሲሄድ የአገሮቹ መንግሥት ግራ ሊጋቡ አይገባም፤›› ያሉት አቶ አበጀ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ በቅርቡ ተግባራዊ የሚደረገው የሰሌዳ ዓይነት የሚገልጸው ተሽከርካሪነታቸውን ብቻ እንደሚሆን አስረድተዋል፡፡

ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያስመዘገበችው የተሽከርካሪ ሰሌዳ መለያ ኢት (ETH) የሚል መሆኑን አቶ አበጀ አስረድተዋል፡፡ ይሁንና አሁን ባለው አሠራር መሠረት ይኼ መለያ ያለበት የተሸከርካሪ ሰሌዳ የሚያገኙት ንብረትነታቸው የፌዴራል መንግሥት የሆኑ፣ ሁለት ወይም ከሁለት በላይ የሆኑ ክልሎችን የሚያገናኝ የንግድ የመንገድ ማመላለሻ ሥራ የሚሠሩ ተሽከርካሪዎች ናቸው፡፡

በሚኒስትሮች ምክር ቤት የፀደቀው ይኼ ረቂቅ አዋጅ፣ የክልል መለያ በሰሌዳዎች ላይ እንዲኖር የሚያዘውን አባሪ እንዲሻር ቢያደርግም፣ በቀጣይ የሚኖረውን የሰሌዳ ዓይነት አይደነግግም፡፡ ‹‹ምን ዓይነት ሰሌዳ ይደረግ?›› የሚለው ከአዋጁ መፅደቅ በኋላ በሚደረግ ጥናት እንደሚወሰን ያብራሩት የሕግ አማካሪው፣ ሰሌዳው ግን ‹‹የኢትዮጵያ ሰሌዳ›› እንደሚባል አስታውቀዋል፡፡

አቶ አበጀ አሁን ባለው የሰሌዳ አሠራር ምክንያት ተሸርካሪዎች ከክልል ወደ ክልል ሲንቀሳቀሱ ‹‹ሥጋት›› እና ‹‹ፍራቻ›› በውስጣቸው ሊፈጠር እንደማይገባ ገልጸው፣ አሁን ባለው የአገሪቱ ነባራዊ ሁኔታ ይኼንን ዓይነቱን ችግር መፍቻ አንዱ መፍትሔ ብሔራዊ ሰሌዳን መተግበር እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

ይሁንና የተሽከርካሪ ሰሌዳው ከየት እንደወጣ ወይም የት እንደተመዘገበ የሚገልጽ መለያ ሙሉ ለሙሉ ይቀራል ማለት እንዳልሆነ የሕግ አማካሪው ጠቁመው፣ ነገር ግን ወደፊት በሚወጣው አዲስ አተገባበር ሰሌዳው የወጣበትን ቦታ የሚገልጸው መለያ የሚቀመጠው ‹‹በተቻለ መጠን›› የትራፊክ ፖሊሶችና የትራንስፖርት ተቆጣጣሪዎች ብቻ እንዲያውቁት በሚያስችል መንገድ ነው ብለዋል፡፡

ረቂቅ አዋጁ በውስጡ ስለ ‹‹ሽግግር ጊዜ›› የሚያትት አንቀጽ እንዳለው ያስረዱት አቶ አበጀ፣ በዚህ መሠረት በሚኒስቴሩ የሚከናወነው ጥናት ተጠናቆ አዲስ አሠራር እስኪተገበር ድረስ ነባሩ አሠራር ተግባራዊነቱ እንዲቀጥል ያዛል ብለዋል፡፡ አዲሱ አሠራር መተግበር ሲጀምር ክልሎች በአዲሱ አሠራር መሠረት የተሽከርካሪ ሰሌዳዎችን መስጠት እንደሚቀጥሉ ተነግሯል፡፡

የመንገድ ትራንፖርት ረቂቅ ከዚህም ተጨማሪ ለውጦችን በውስጡ የያዘ ሲሆን፣ አንደኛው ጉዳይ የአዲስ አበባና የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደሮች ትራንስፖርት ቢሮዎችን የሚመለከት ነው፡፡ የቀድሞው ገዥ ፓርቲ ኢሕአዴግ በ1997 ዓ.ም. ምርጫ በአዲስ አበባ ከተሸነፈ በኋላ፣ አዲሱ ፓርላማ ከመግባቱ በፊት ያወጣቸው ሕጎች እንደነበሩ ያስታወሱት አቶ አበጀ፣ ከእነዚህ ሕጎች መካከል የትራንፖርት አዋጅ አንዱ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ በጊዜው የወጣው አዋጅ የአዲስ አበባና የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደሮች የትራንፖርት ቢሮ ተጠሪነታቸው ለፌዴራል መንግሥት ሆኖ፣ ራሳቸውን የቻሉ ቢሮዎች ሳይሆን ቅርንጫፍ እንዲሆኑ የሚያዝ ነበር፡፡

አሁን የተዘጋጀው ረቂቅ አዋጅ ይኼንን ሕግ ሽሮ የከተማ አስተዳሮቹ ትራንስፖርት ቢሮዎች ራሳቸውን ችለው የከተማ አስተዳደሩ አንድ መዋቅር እንዲሆኑ ያደርጋል፡፡ የድሬዳዋ ከተማ ትራንፖርት ቢሮ አሁንም የፌዴራሉ ቅርንጫፍ ሲሆን፣ የአዲስ አበባ ከተማ ግን ሕጉ ሳይሻሻልም የራሱን ትራንስፖርት ቢሮ ከፍቶ በመንቀሳቀስ ላይ መሆኑን የሚኒስቴሩ የሕግ አማካሪ አስረድተዋል፡፡ ረቂቅ አዋጁ ሲፀድቅ ለአዲስ አበባ ትራንፖርት ቢሮ ሕጋዊ መሠረት ይሰጠዋል ተብሏል፡፡

Check Also

አማራና ትግሬ ተስማሙና ኦሮሙማን መክቱ። – ሞጣ ቀራንዮ

https://fb.watch/f-ipLpwPrZ/ Related Posts:አማራና ኦሮሞ አትጣሉ። ተዋደዱ !አማራና ትግሬ ወደ አዲስ አበባ እንዳይገቡ የኦሮሞ ክልል አስተዳደር …

ማስጠንቀቂያ ለከንቲባ አዳነች እቤቤ!

Related Posts:የጃዋር ሞሃመድ የዜግነት አወዛጋቢ ጉዳይ. ጃዋር ማስጠንቀቂያ ተሰጠው !

Multi threaded Redundant Dedicated Server in USA and in Europe.