Breaking News
Home / Amharic / የአማራ ማህበራት የጋራ ትብብር – በጀርመን በወቅታዊ ጉዳይ ላይ የተሰጠ መግለጫ፣

የአማራ ማህበራት የጋራ ትብብር – በጀርመን በወቅታዊ ጉዳይ ላይ የተሰጠ መግለጫ፣

“ለፍቅር ቢያገቧት ለጸብ አረገዘች” ሆነና ፡ የአማራ ህዝብ በተረኛ ገዥዎቹ መከዳቱን እየተመለከትን ነው፡፡ የ”ትሕነግ” የበኸር ልጅ “አዴፓ” ዛሬም እንደ ትላንቱ ሁሉ የአማራን ህዝብ መብትና ጥቅም ለተረኛ ዘውጌዎች አሳልፎ የመስጠትና አንገት የማስደፋት ተልዕኮውን በብቃት እየተወጣ ነው፡፡ ስለሆነም፣ የህዝባችን ህልውናው ዛሬም አጣብቂኝ ውስጥ እንደገባ ነው “ትላንት አማራ አልነበርኩም አሁን ተለውጬ አማራ ሆኛለሁ” ያለን ብአዴን “የጎባጣ አሽከር አጎንብሶ ይሄዳል” ሆነና፣ በለውጥ ስም ስያሜውን ቀይሮ ሌላ ታሪካዊ ስህተት በህዝባችን ላይ ሲፈጽም እየተመለከትን ነው፡፡ አዴፓ ሠፊ ታሪካዊ ህዝብ እየመራ ሳለ፣ የፀረ አማራ ሃይሎች የጥፋት ማስፈጸሚያ ተቋም ሆኖ መቀጠሉ፣ አሳዛኝ ብቻ ሳይሆን አሳሳቢም ነው፡፡ ቆሜለታለሁ የሚለውን የአማራን ህዝብ መብትና ጥቅም አሳልፎ ለባላንጣዎቹ በመስጠት፣ ዳግም በበዳይነት ጎራ መቆሙ፣ ከስህተት ያለመማሩን ያረጋግጣል፡፡ “ድመት መንኩሳ አመሏን አትረሳ” እንዲሉ፣ የለውጥ አራማጅ ነኝ ባዩ ቡድን፣ ቃሉን አጥፎ ፡ አማራውን ይበልጥ የከፋ የፖለቲካ ቀውስ ውስጥ እየከተተው ይገኛል፡፡

በተለይም አዴፓ ህዝብ የሰጠውን እድል ተጠቅሞ፣ ስህተቱን ከማስተካከልና ከማረም ይልቅ፣ መንደር ውስጥ ለመደበቅ በመሞከር ሌላ ወንጀል በአማራው ህዝብ ላይ እየሰራ ነው፡፡ተለጣፊ አደረጃጀቶችን እያስፋፋ፣ የወጣቱ እንቅስቃሴ ለማፈን እያደረገ ያለውን መሰሪነት አጥብቀን እንቃወማለን፡፡ በ1983 ዓ.ም እንደተደረገው፣ ዛሬም የዶ/ር አብይ ብልጽግና ፓርቲ አማራውን ከሃገሪቱ የፖለቲካ ተሳትፎ የማግለል ሴራውን አጠናክሮ የቀጠለበት መሆኑን ሁሉም ሊያውቅ ይገባል፡፡

አዴፓ ከፌዴራል ዘውገኞች ጋር በማሴር በማናለብኝነት በህዝባችን ላይ እየፈጸመ ያለው ወታደራዊ ወረራ፣ ስርዓቱ ወደ ለየለት አምባ ገነንነት እየሄደ ስለመሆኑ ጉልህ ማሳያ ነው፡፡ ጽንፈኛ ሃይሎች፣ በኢትዮጵያዊነት ካባ ስር ተጠልለው ሃገር የማፍረስ ተልዕኮ ተክነውበታል፡፡ በታሪክ አማራ ጠንካራ በነበረበት ወቅት ኢትዮጵያ ተከብራ ኖራለች፣ አማራው በተዳከመበት ወቅት ደግሞ ህልውናዋ ፈተና ውስጥ ሲገባ በታሪክም፣ ዛሬም ተመልክተናል፡፡ አሳዛኙ ነገር ግን አማራን የመረዘው የውስጥ እባብ የኢትዮጵያ ቤዛ አድርጎ የመወሰዱ የሞኝነት ፈሊጥ ከፊሉን የአማራ ተወላጆች ጨምሮ፣ ሃገር ወዳድ ነኝ ባዩ ወገን ሁሉ ሊያጤነው አለመቻሉ ነው፡፡

የአካባቢውን ጸጥታና ሠላም ለማስከበር በሚል የህግ ሽፋን፣ በጎንደር፣ በጎጃም፣ በወሎ፣ በሰሜን ሸዋ “ፋኖ” የአማራ ህዝባዊ ሠራዊትን ለመድፈቅ፣ አዴፓና የዶ/ር አብይ አስተዳደር ያዘመቱት፡ የመከላከያ ሠራዊት በህዝባችን ላይ ከፍተኛ ሰብዓዊ ጥፋት በማድረስ ላይ መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ እርምጃው የኮረና ቫይረስ የፈጠረውን አጋጣሚ ተገን አድርጎ በመውሰድ እየተደረገ ያለ እንደመሆኑ መጠን፣ በአማራው ላይ እየደረሰ ያለው በደልና ግፍ ድርብ ድርብርብ አድርጎታል፡፡ በዚህ የጥፋት እርምጃ በዓስሮች የሚቆጠሩ ሰላማዊ ሰዎች ተገድለዋል፣ ቁስለኛ የሆኑትን ቤት ይቁጠራቸው፣ በርካቶች ቤት ንብረታቸውን ጥለው እየተሰደዱ ነው፡፡ አጥፊና ጤነኛው ሳይለይ፣ በጅምላ እንዲህ ያለ ሃላፊነት የጎደለው ተግባር፣ የአማራን ተፈጥሯዊ እራስን የመከላከል መብት የሚጎዳ ብቻ ሳይሆን፣ ባህላዊውን የአርበኝነት ስልት የማጥፋት ሴራ ነው ብለን እንፈራለን፡፡ በዚህ ከመቀጠልም፣ አማራን በማያባራ የርስ በርስ ደም አፍሳሽ ትርምስ ወስጥ የሚከት ሃላፊነት የጎደለው እርምጃ በመሆኑ፣ አጥብቀን እንቃወማለን፡፡ ከእንዲህ ያለ ታሪካዊ ስህተት መንግስትም እንዲታቀብ አጥብቀን እንጠይቃለን፡፡

በሌላም በኩል፣ ሰሞኑን በመተከል በአማራ ተወላጆች ላይ የተደረገው ኢሰብዓዊ የዘር ጭፍጨፋ ሳቢያ ከ21 በላይ አማሮች ለሞት ተዳርገዋል፡፡ በአርባ ጉጉም በተመሳሳይ 6 ሰዎች ተገድለዋል፡፡ ይህ ሁሉ አስከፊ ድርጊት ላለፉት 30 ዓመታት በተደጋጋሚ፣ በአስከፊና ዘግናኝ ሁኔታ በህዝባችን ላይ ሲደርስ የቆዩ መሆኑ አልበቃ ብሎ፣ ሌላ ፈታኝ የህልውና አደጋ ውስጥ እያስገባውና እዲጠቃ እያደረገው በመሆኑ፣ ድርጊቱን እናወግዛለን፡፡

መንግስት አስፈላጊውን ሁሉ እርምጃ ወስዶ አማራውን ከጥቃት እንዲከላከልና ማህበራዊ ህልውናውን እንዲያረጋግጥ አጥብቀን እንጠይቃልን፡፡
ከ2500 በላይ የአማራ ተወላጆች ከአዲስ አበባ እየተጋዙ ወደ ባህርዳር በግፍ መወሰዳቸውን አጥብቀን እንቃወማለን፡፡ ከአማራ የጸዳች አዲስ አበባን የመፍጠር የዘረኞች ትልም፣ የአማራውን የዜግነት መብትና ሃገራዊ ባለድርሻነት የሚገፍ ኢሰብዓዊ ተግባር ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት ድርጊቱ መፈጸሙ ይበልጥ ምሬትን የፈጠረ ተግባር ነው፡፡ አማራው ይበልጥ ለኮሮና ወረርሽኝ ተጋላጭ በማድረግ፣ እንዲያልቅ የማድረግ ኢሰብዓዊነት ተግባር እየተፈጸመበት በመሆኑ፣ መላው የኢትዮጵያ ህዝብ ሊያውቀውም ይገባል፡፡ ይህን የጥፋት ተግባር የዶ/ር አብይ አስተዳደር እንዲያስቆምና የእርምት እርምጃ እንዲወስድም አጥብቀን እንጠይቃለን፡፡

“አዴፓ” የአማራ ህዝብ ዳግም የፖለቲካ ወኪል ድርጅት እንዳይኖረው በማሴር “አብንን” ለመድፈቅ እየሄደበት ያለው የጥፋት መንገድ ሁሉም አማራ ሊያውቀውና በንቃት ሊከታተለው የሚገባ ጉዳይ ነው፡፡ የአማራ ወጣቶች በነጻነት እንዳይደራጁና ለጋራ መብትና ልማት በጋራ እንዳይቆሙ የሚያደረገውን አፈና አጥብቀን እንቃወማለን፡፡ ወጣቱንም ሆነ “አብንን’ በጽንፈኝነት ለመፈረጅና ለማጥቃት እየተቀነባበረ ያለው ሴራ፣ በቅርብ የምንከታተለው ሲሆን አጥብቀን የምንቃወመው ነው፡፡ በጥቅሉ አማራን ለመድፈቅ የሚደረገውን ሴራ ለመመከት፣ መላው ህዝባችን ከምንጊዜውም በላይ አንድ ላይ በመቆም፣ በህጋዊና ሠላማዊ መንገድ እንዲከላከል ጥሪ እናቀርባለን፡፡ የብልጽግና ፓርቲም ይህን አውቆ በህዝባችን ላይ የከፈተውን የጥፋት ዘመቻ እንዲያቆም እንጠይቃለን፡፡

Check Also

የፓርላማ ተወካዮች ፀረ አማራ የሆኑ ዝርዝር ከነስልክ ቁጥራቸው

Related Posts:የህዝብ ተወካዮች ስልክ ቁጥር ዝርዝር።ይሄ ፀረ ኢትዮጵያ የሆነው ሀንጋሳ ኢብራህም የሚባለው ኦህዴድን ብልጥግናን ወክሎ …

የህዝብ ተወካዮች ስልክ ቁጥር ዝርዝር።

ሼር ይደረግ! የህዝብ ተወካዮች የምክር ቤት በነገው እለት በአማራ ህዝብ ላይ ያወጀውን የእልቂት አዋጅ ለማፅደቅ …

Multi threaded Redundant Dedicated Server in USA and in Europe.