Breaking News
Home / Amharic / የሰንደቅ አላማ (ባንዲራ) ታሪክ

የሰንደቅ አላማ (ባንዲራ) ታሪክ

ስለ ሰንደቅ ዓላማ ትርጉም ስናወራ ሰንድቅ ዓላማ ማለት በዘንግ ወይም በመስቀያ ያለ ሰንደቅ ማለት ነው፡፡ መስቀያው ዓላማ ሲባል የሀገር ዓርማ የሆነው ባለቀለሙ መለያ ምልክት ደግሞ ሰንደቅ ይባላል፡፡ የሚለው አንዱ ሲሆን ሌላኛው ትርጉሙ ደግሞ ሰንደቅ ዓላማ የሚባለው ባለቀለሙ የመለያ ምልክት ብቻ እንጅ መስቀያውን አይጨምርም ሰንደቅ ዓላማ መባሉም ሰንደቁ የራሱ የሆነ ዓላማ እንዳለው ለማመልከት ነው የሚሉም አሉ፡፡ የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ የመንግሥት ሰንደቅ ከመሆኑ በፊት ከኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ንዋዬ ቅድሳት አንዱና እንዲያውም የመጀመሪያው የቤተክርስቲያን ሰንደቅ ነበር፡፡ በቤተክርስቲያን እነዚያ ሦስት ቀለማት አረንጓዴ ቢጫ ቀዩ ወይም ቀይ ቢጫ አረንጓዴው ቀለማት በንዋዬ ቅድሳቶቿ ሁሉ ላይ ከብራና መጻሕፍቶቹ እስከ መንበረ ታቦታተሕጉ ድረስ ይገኛል፡፡

ከጥንታዊ የብራና መጻሕፍት አንሥቶ እስከ ጉልላቷና መንበረ ታቦቷ ድረስ ከጥንት ጀመሮ የእነዚህ ቀለማት ማኅተም በተለያዩ መልኩ አሠራሩና ጥበባዊ ስልቱ እንዲያርፍበት ይደረጋል፡፡ የዚህ ምክንያቱ ደግሞ በመጽሐፍ ቅድስ በዘፍ 9÷8-17 ላይ እንደተገለጸው እግዚአብሔር በኖሕ በኩል ለሰው ልጆች ሁሉ ዓለምን ዳግመኛ በጥፋት ውኃ ላያጠፋት ቃል ሲገባለት ለገባው ቃል ምልክትና ምስክር ትሆን ዘንድ “ቀስቴን በደመና ላይ እዘረጋለሁ የምሕረት የቃል ኪዳን ምልክት ትሁን” እንዳለው እናያለን፡፡

አንዳንድ ሰዎች ታዲያ ሰንደቁ ቀስተ ደመና ከሆነ ለምን ሦስት ቀለማት ብቻ ሆነ? በቀስተ ደመና ውስጥ ያሉት ቀለማት ሰባት ናቸውና የሚሉ አሉ፡፡ እርግጥ ነው አትኩረን ላየነው በቀስተ ደመና ውስጥ ያሉ ቀለማት ሰባት ናቸው፡፡ ነገር ግን አራቱ ቀለማት የሚፈጠሩት በውሕደትና በውርርስ እንጅ እንደ ሦስቱ ቀለማት ማለትም እንደ ቀዩ ቢጫውና አረንጓዴው በራሳቸው ህልው ሆነው አይደለም ቀዩ ከቢጫው ቢጫው ከአረንጓዴው ጋር ባለው መጋጠሚያ መጋጠሚያቸው ላይ በንክኪው ውሕደት ሲፈጥሩ የሚፈጠሩ ሁለት እንዲሁም ከቀስተ ደመናው ላይና ታች ከሰማዩና ከመሬቱ ቀለማት ጋር ባለው መወራረስ ደግሞ ሌላ ሁለት የሚፈጠሩ ናቸው፡፡ በድምሩ 4ቱ ቀለማት ከአረንጓዴው ከቢጫውና  ከቀዩ ውጭ ያሉት በራሳቸው ህልው የሆኑ ሳይሆኑ በእነዚህ በሦስቱ ቀለማት ተጽዕኖ የሚፈጠሩ በመሆናቸው ቤተክርሲቲያን ሦስቱን ዋነኛ የቀስተ ደመናውን ቀለማት ብቻ ልትወስድ ችላለች፡፡

በመሆኑም የቀስተ ደመናው ቀለማት በጉልህ የሚታዩት ቀይ ቢጫ አረንጓዴ ሦስቱ ቀለማት ናቸው እንጅ ሰባት ቀለማት አይደሉም ማለት ነው፡፡ በተጨማሪም  ሦስቱ  ቀለማት ሦስት መሆናቸው በቤተክርስቲያን ካላቸው የምሥጢር ትርጉም አንዱን ብቻ ስጠቅስ የምሥጢረ ሥላሴ ምሳሌ መሆኑ ወይም መሆናቸው ነው ትላለች ቤተክርስቲያን፡፡ ማለትም ሥላሴ (እግዚአብሔር) አንድም ሦስትም ናቸው ወይም ነው የሚለውን ምሥጢረ ሥላሴን ለማጠየቅ ነው፡፡ ቀስተ ደመና ከቃል ኪዳን ምልክትነቱም በላይ የልዑል እግዚአብሔር የክብሩ መገለጫም ነው፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ዮሐንስና ነቢዩ ሕዝቅኤል በየራእዮቻቸው ልዑል እግዚአብሔር በክብርና በሚያስፈራ ግርማ በዙፋኑ ላይ ሆኖ ዙሪያውን በሚያምርና ኅብር ባለው የቀስተ ዳመና ጸዳል ተከቦ ተመልክተውታል፡፡ ራዕ ዮሐ 4÷2-3 ትን ሕዝ 1÷26-28

አንዳንድ ሰዎች እነኝህን ቀለማት ከጥንት ጀምሮ ለመጠቀም በዚያ ጊዜ ቀለም ነበረ ወይ? ሲሉ የሚጠይቁ አሉ ለእነኝህ ሰዎች ልነግራቸው የምወደው ነገር ቢኖር በዓለም 1500 ዘመን ያለው የመጀመሪያው ሙሉ የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ በሥዕል ተሥሎ የተገለጸው በእኛ እንደሆነና አሁንም ድረስ እንዳለ ላስታውሳቸው እወዳለሁ፡፡

እንግዲህ እግዚአብሔር የቃል ኪዳን ምልክት ነው ወይም ናቸው ያላቸውን በጉልህና በግልጽ የሚታዩትን በራሳቸው ህልው የሆኑትን ሦስት ቀለማት በመውሰድ ቅድስት ቤተክርስቲያን ከእግዚአብሔር እንደተሰጣት የቃል ኪዳን ምልክቷ አድርጋ በመውሰድ ለተለያዩ መንፈሳዊ አገልግሎት ትጠቀምበታለች፡፡ ለምሳሌ በሀገር ላይ አንዳች ችግር፣ መዓት፣ ቁጣ በሚከሰትበት ጊዜ ማለትም ጦርነት፣ ረሀብ፣ ድርቅ፣ በሽታ፣ ቸነፈር የመሳሰሉት ችግሮች ሲፈጠሩ ምንም እንኳ ቀይ ቢጫ አረንጓዴው ትእምርተ ኪዳኑ (የቃል ኪዳኑ ምልክት) የተሰጠው “መላ ዓለምን የሚያጠፋ የጥፋት ውኃ ዳግመኛ በሰው ልጆች ላይ ላያመጣ” ቢሆንም ይህችን የቃል ኪዳን ምልክት አንድ ጊዜ የምሕረት የቃል ኪዳን ምልክት ብሏታልና እነዚህ ችግሮች በሚከሰቱበት ጊዜም በምህላ ጸሎት (ወር በገባ ከ1-7 ባሉት ቀናትና ከላይ የተገለጹት ችግሮች በሀገር ላይ ሲከሰቱ የሚጸለይ የጸሎት ዓይነት) ጊዜ ፈጣሪን ከቁጣህ ተመለስ፣ በምሕረትህ አስበን፣ በቸርነትህ ጎብኘን፣ ቃልኪዳንህን አስብ  ለማለትና ለምሕረት የገባውን ቃል አስቦ አስታውሶ ምሕረት እንዲሰጠን ለማድረግ በጸሎቱ ሰዓት ትእምርተ ኪዳኑን ከሥዕለ አድኅኖና ከመስቀሉ ጋር ተይዞ በዐውደ ምሕረት ላይ እየተወጣ ቤተክርስቲያን በዚህ መልኩ ከጥንት ጀምሮ ስትገለገልበት እንደቆየች በአድዋ ጦርነት ጊዜ በተንቀሳቃሽ ድንኳን እየተቀደሰ አብሮ ዘምቶ ከነበረው የቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን ድሉን እንዳገኙ ዐፄ ምኒልክ ቀይ ቢጫ አረንጓዴውን ሰንደቅ (ትእምርተ-ኪዳን) አንሥተው ከዛሬ ጀምሮ ይህች ሰንደቅ የኢትዮጵያ ሰንደቅ ትሁን ብለው እዛው ካሉበት አድዋ አወጁ፡፡ በእርግጥ በአዋጅ በይፋ አይሁን እንጅ ከዚያ ቀደም የነበሩ ነገሥታትም በጣም ከጥቂቶቹ በስተቀር ካህናት ማለትም ቢያንስ ዲያቆን ያልነበረ የለምና በዚህ ቅርበታቸው ይህንን ትእምርተ ኪዳን (ሰንደቅ) እንደ ሀገር ሰንደቅ አድርገው ይጠቀሙበት እንደነበረ ይታወቃል፡፡ ቀረብ ያሉትን ለማንሣት ዐፄ ቴዎድሮስን ከሳቸውም በኋላ ዐፄ ዮሐንስ 4ኛንም መጥቀስ ይቻላል፡፡

እናም ዐፄ ምኒልክ ያንን አዋጅ ካወጅ ጊዜ ጀምሮ ቀይ ቢጫ አረንጓዴ ቀለማት ትእምርተ ኪዳን የመንግሥት ወይም የሀገራችን ይፋዊ ምልክት ዓርማ ወይም መለያ ሰንደቅ ሆኖ እንዳጋጠመ ማለትም አንድ ጊዜ እንደመጀመሪያው አደራደር ቀይ ቢጫ አረንጓዴ ወደ ኋላ ደግሞ አረንጓዴ ቢጫ ቀይ እየሆነ በዓላማ ወይም በዘንግ ሲሰቀል ቆይቶ መጨረሻ ላይ አረንጓዴ ቢጫ ቀይ በሚለው አደራደር ጸና፡፡ መሆን የነበረበት አደረደር ግን የመጀመሪያው ቀይ ቢጫ አረንጓዴው ነበር ምክንያቱም የዚህ ሰንደቅ ምንጭ ምሳሌ ወይም መሠረት  የሆነው የቀስተደመናው አደራደሩ እንዲሁ ነውና፡፡ በመሆኑም የይዘትና ትርጉም መፍለስ እንዳይከሰት ወደ ነበረበት ቢመለስ መልካም ይመስለኛል፡፡

በነገራችን ላይ የዚህን ሰንደቅ የቃል ኪዳን ምልክትነት የምትጠቀም ወይም የምትገለገል የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ብቻ አይደለችም ከመቸ ጀምሮ እንደሆነ ባይታወቅም ነገር ግን ያመኑበት ዘመን እንደ እኛ በሁለቱም የኪዳናት ዘመን ባለመሆኑና በሐዲስ ኪዳን ከሐዲስ ኪዳንም ሩቅ የሚባል ካለመሆኑ የተነሣ ቅርብ እንደሚሆን ቢገመትም ከላቲን አብያተክርስቲያናት ቀደምት የሆኑቱ በተለይም የላቲን አሜሪካዎቹ ይሄንን ትእምርተ ኪዳን የቃል ኪዳን ምልክትነቱን በማወቅ በአረንጓዴ ቢጫ ቀይ አደራደር የሚጠቀሙበት ነበሩ አሉም፡፡

እንግዲህ የሰንደቃችን ምንጭና መሠረቱ ይሄ ሆኖ የኢትዮጵያ መንግሥትም ከቤተክርስቲያን ተውሶ ይፋዊ የመንግሥትም ሰንደቅ ማለትም እጅግ የምንወዳትንና ውድ መራር ዋጋ መሥዋዕትነት የከፈልንላትንና የምንከፍልላትን ሀገራችንን ኢትዮጵያንና ክቡሩን ውዱን ጀግናውንና ባለታሪኩን ሕዝቧን እንድትወክል ከተደረገ በኋላ የተለያዩ የኢትዮጵያ መንግሥታት የየራሳቸውን መለያ ዓርማዎቻቸውን በየዘመናቸው እላዩ ላይ ሲለጥፉበት ቆይተዋል፡፡

ከዐፄ ኃይለሥላሴ ቀዳማዊ ጀምሮ ያለውን ብናይ ዐፄ ኃይለሥላሴ የክርስቶስ ምሳሌ የሆነውን በነቢያት ተነግሮ የነበረውን ቃልና ሥዕል “ሞዓ አንበሳ ዘእም ነገደ ይሁዳ” (አሸናፊ አንበሳ ከይሁዳ ነገድ) ይወጣል የሚለውን ቃል ከነሥዕሉ ዘውድ የደፋ አንበሳ መስቀል አስይዘው ሥለውበት ነበር፡፡ ጥቂት የማይባሉ ሰዎች ከዕውቀትና ግንዛቤ ማነስ የተነሣ ይህን የአንበሳ ምልክት ጃንሆይ እራሳቸውን እንዲወክል ያደረጉት እንደሆነ አድርገው ያስባሉ፡፡ ሲጀመር የአንበሳው ምልክት በዐፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመን የተጀመረ አይደለም ከሽዎች ዓመታት በፊት ጀምሮ የሀገራችን መንግሥታት ብሔራዊ ምልክት ሆኖ የኖረ ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስና ሌሎችም የቤተክርስቲያን ቅዱሳት መጻሕፍት ይህ ቃል ማለትም “ሞዓ አንበሳ ዘእም ነገደ ይሁዳ” የሚለው ቃል ለአማልክት አምላክ ለነገሥታት ንጉሥ ለክርስቶስ የተነገረ እንደሆነ ገና ክርስቶስ እንኳን ከመወለዱ ከሽህ ዓመታት በፊት ጀምሮ  በትንቢት ሲነገር የቆየ ከተወለደም በኋላ ትንቢቱ መፈጸሙን እየተነተኑ አስረድተዋል፡፡ ከዐፄ ኃይለ ሥላሴ ቀዳማዊ በፊት ዐፄ ምኒልክ ዳግማዊ ከዚያም በኋላ ዐፄ ኃይለ ሥላሴ ቀዳማዊ እንደ አማኝነታቸው ይህንን ቃል ከምሥጢሩ ጋር ለማስማማት ከትእምርተ ኪዳኑ (ከሰንደቁ) ላይ እንዲሠፍር አደረጉ፡፡ ነገር ግን “ሞዓ አንበሳ ዘእም ነገደ ይሁዳ” የሚለው ቃል ባይኖር ኖሮ አንበሳ ለሽዎች ዓመታት ለሰሎሞናዊው ሥርዎ መንግሥት የነገሥታቶቻችን ወይም የሀገራችን ብሔራዊ ምልክት የነበረ በመሆኑ ጃንሆይም እንደ ቀደምቶቻቸው ሁሉ አንበሳውን ያደረጉት እራሳቸውን እንዲወክል ነው ቢባል ሊያስኬድ ይችል ነበር፡፡

ደርግ ሲመጣም መስቀሉንና ዘውዱን በመተው አንበሳውን ጭንቅላቱን ብቻ ከሌሎች ዓርማዎቹ ጋር ማለትም የአክሱም ሐውልት፣ የዘንባባ ዝንጣፊ፣ የስንዴ ዛላ፣ኢንዱስትሪን (ምግንባብን) የሚወክል የማሽን (የማሳልጥ) ጥርስ፣ ጦርና ጋሻንም አቀናጅቶ ለጥፎበት ነበር፡፡ ለብቻው በፓርቲው ሰንደቅ ላይ ደግሞ ማጭድና መዶሻ ለጥፎበት ነበር፡፡ በመንግሥታዊ ድርጅቶች ደረጃ ደግሞ ልክ በጃንሆይ ዘመን ሲጠቀሙበት በነበረው መልኩ ማለትም አንበሳው እንዳለ ሆኖ የየድርጅቶቹን አገልግሎት የሚወክል ምልክቶች አብረውት ሆኖ ይገለገሉበት በነበረውም መልኩ በደርግ ዘመንም ከደርግ በኋላም በኢሕአዴግ ዘመንም ቀጥሎ እያለ ይህ የአንበሳ ብሔራዊ ምልክትነት ወይም መለያነት በመንግሥት ድርጅቶች ደረጃም ቢሆን በኢሕአዴግም መቀጠሉ ዓይናቸውን ያቀላው ያንገበገባቸው ወገኖች %ረ ምን ወገኖች ጠላቶች ልበል እንጅ ምክንያቱም ሥራቸው የባዕድ የጠላት እንጅ የዜጋ አይደለምና፡፡

እናም እነኝህ ሰዎች ይህን የአንበሳ ምልክት ከመንግሥት ድርጅቶች በተለይም ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ምልክትነትቱ እንዲነሣና እንዲቀየር ጠይቀው ከአቶ መለስ ጋር ተስማምተው እንደነበርና ውይይታቸውም በኢቴቪ. ተላልፎ እንደነበረ ይታወሳል፡፡ ነገር ግን ብዙ ምሁራን የሀገር ልጆች በጉዳዩ ላይ በመረባረባቸውና ይሄንን ማድረግ ማለት ምን ማለት እንደሆነ፣ ታሪክ ማለት ተወደደም ተጠላ የነበረውን ጠብቆ ማቆየትና ባለውም ላይ መጨመር እንጅ የነበረውን ማጥፋት ማውደምና በቦታው ሌላ መተካት እንዳልሆነ፣ ለሽዎች ዓመታት ከማንነታችን ጋር የተሳሰረን መለያ ያልገባቸው ወይም ለጠላት ያደሩ ማንነታቸውን ለጥቅም የሸጡ ግለሰቦች ስለጠየቁ ብቻ ይወገድ ተብሎ የሚወገድ ሊሆን እንደማይገባ፣ እነኝህ ከላይ የተገለጹትን ቁምነገሮችንና ማስገንዘቢያዎችን መረዳት ካቃተ ወይም ካልተቻለና በግድ መነሣት አለበት የሚባል ከሆነ ደግሞ ይነሣ የሚሉ ጥቂት ወገኖች እንዳሉ ሁሉ እንዳይነሣ  እንዲጠበቅልን የምንፈልገው ደግሞ ብዙዎች አለንና የሕዝብ ውሳኔ ሳይሰጥበት መነሣት እንደማይኖርበት ይሄን ሁሉ ነገር ግንዛቤ ውስጥ በማስገባት በማን አለብኝነት የሚነሣ ከሆነ የአየር መንገዱ ዋነኛ ደንበኛ የሆንን እኛ በውጭ የምንገኝ ኢትዮጵያዊያን ይህ ዓርማ እንደተነሣ አየር መንገዱን መጠቀማችንን ወዲያውኑ የምናቆም መሆናችንን እናረጋግጣለን፡፡ የሚል የጸና አቋም በመያዛቸውና በመረባረባቸው፣ አየር መንዱም ከገበያውና ከጥቅሙ አንፃር ይህ ቢደረግ ሊደርስበት የሚችለው ኪሳራ ከባድና ምናልባትም እስከመዘጋት ሊያደርሰው እንደሚችል በመግለጹ መወገድ ጀምሮ የነበረው አንበሳ ሊተርፍ ቻለ፡፡ “እልህ ምላጭ ያስውጣል” ይባላልና መጠኑና ድምቀቱ ግን አነስና ደብዘዝ እንዲል ተደረገ፡፡

ከሌሎች መንግሥታዊ ድርጅቶች ግን ለምሳሌ ከቴሌ ደኅና ከርሞ ቆይቶ አሁን በቅርቡ  እንዲወገድ ተደርጎ በሌላ ምልክት ተቀይሯል፡፡ አንበሳው ከጥንት ጀምሮ እስከ ደርግ ዘመን ድረስ ለብዙ ሽህ ዓመታት ከነበረበት ብሔራዊ ምልክትነቱ ግን ያለ ምንም እዚህ ግባ የሚባል ምክንያት በኢሕአዴግ ዘመን እንዲቀር ተደርጓል፡፡ የኢሕአዴግ (የኢፌዲሪ) “መንግሥት” ሰንደቁ ላይ የለጠፈውና ምልክቴ የሚለው ደግሞ ባለ አምስት ጎን ኮከብ ነው፡፡

እዚህ ላይ ሰዎች ብዙ ጊዜ ሲስቱት የማስተውለው ጉዳይ አለ ለቅርስ ያለን ግንዛቤ እጅግ አናሳና የተዛባም ነው፡፡ ቅርስ ምንጊዜም ቅርስ ነው ዛሬ ላይ አቋም አመለካከታችን፣ ሃይማኖታችን  ወዘተ ተቀየረ ተለወጠ ተብሎ ትናንት ከነበረን ማንነት የወጣን የተለወጥን ወገኖች ትናንት የነበርንበትን ማንነታችንን መለያችንን ይቅር ይውደም ይጥፋ ማለት አይኖርብንም፡፡ እንኳንና ያንን ማንነት መለያ ይዞ ዛሬም የሚጠቀምበትና የሚፈልገው ወገን እያለ ቀርቶ ባይኖርም እንኳ  የሁላችምን አሻራ ነውና ይጥፋ ይወገድ ማለት አይኖርብንም፡፡ የሠለጠነው ዓለምም የሚያስበውና  የሚያደርገውም ይህንኑ ነውና፡፡ ቢቻል ቢቻል የነበረንን ማንነት መለያ እሴት ባንለቅ ባንተው ብንጠብቅ ተወናብደን በተለያዬ መንገድ ከማንነታችን የኮበለልነውም ብንመለስ መልካም ነው፡፡ ነገር ግን በአንድም በሌላም ምክንያት በመጥፎ የታሪክ አጋጣሚዎች የማንፈልገው ነገር ተከስቶ የአቋም አመለካከት፣ የሃይማኖት ወዘተ ልዩነቶች በመሀከላችን መከሰቱ ግድ ሲሆን ግን ልዩነቶቻችን እንደተጠበቁ ሆነው ቅርሶቹ ግን ቢያንስ ቢያንስ በዜግነታችን ወይም በኢትዮጵያዊነታችንና በትናንቱ ማንነታችን የኢትዮጵያ የሆኑ ቅርሶች የጋራ ናቸውና እኩል ልንቆጭ እኩል ልንቆረቆር እኩል ንልንንከባከብ ባለአደራነቱ እኩል ሊሰማንና ልንሞትላቸው ያስፈልጋል ይገባልም፡፡

እንደ አንድ ሀገር ሕዝብ የሀገራችንን የጋራ ጥቅሞች የምናሥተዳድርበት የጋራ መግባቢያ (code of conduct) ሊኖረን የግድ ያስፈልጋል፡፡ ከዚህ ተቃራኒ አስተሳሰብ ያለው ዜጋ ቢያጋጥማቹህ ይሄንን ሰው የተስተካከለ አቋም እስኪይዝ ድረስ ሳትታክቱ ምከሩ አስተምሩ ጨርሶ የማይመለስ ከሆነ ግን ይሄ ጠላት እንጅ ወገን አይደለምና ደሙ በእኔ ይሁን አደራ እንዳትምሩት ሳይቀድማቹህ ቅደሙት፡፡ አሁን ካለንበት ዘመን ወደ ኋላ እየቃኘን እየተጓዝን ብንሄድ ኢትዮጵያዊያንን ተቀራምቶ አሁን ኢትዮጵያን ሞልቷት ያለው የባዕዳን ባሕልና ሃይማኖት እየተንጠባጠበ ይቀርና መጨረሻላይ አንድ ሃይማኖትንና ሀገር በቀል የሆነ ኢትዮጵያዊ ባሕልን ብቻ ታኛላቹህ፡፡ ጀምበር ጠልቃ በወጣች ቁጥር በሚፈጠሩት አዳዲስ ከፋፋይ ነገሮች ሁልጊዜ አዲስ ሀገር፣ አዲስ ማንነት፣ አዲስ ሃይማኖት፣ አዲስ ምንትስ እየተያዘ ሀገርና ማንነት ሊገነቡ አይችሉም በዚህ መልኩ የተገነባ ሀገርም የለም ኖሮም አያውቅም፡፡

እንግዲህ ይሄንን ሐሳብ ያዙና ለቅርሶቻችን ያለንን ግንዛቤ ገምግሙ፡፡ እራሳቹህን ታዘባቹህት እንዴ? አይ ይሄ የአማራ ነው የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ፣ ኤዲያ ይሄ የሱማሌ ነው የእስላም የሚል ጠባብና የተሰነካከለ ደካማና የተሳሳተ ሐሳብ መጣባቹህ እንዴ? በሉ እንግዲህ ይሄ ፍጹም የተሳሳተ አስተሳሰብ፣ አጥፊ አመለካከት፣ አውዳሚ ግንዛቤ ነውና ከየጭንቅላቶቻቹህ እያወጣቹህ ጣሉ፡፡ ይሄኔ ነው አንድነት ያለው ሕዝብ፣ ሰላማዊት ሀገር፣ ሉዓላዊ ማንነት፣ የተጠበቀ ቅርስ፣ አስደናቂ መገለጫ፣ ሥር የያዘ ሥልጣኔ፣ ዘመናትን የተሻገረ ታሪክ የሚኖረን፡፡ የኛ የሆነውን የኛ ባልሆነው ለውጠን ጭራሽም የኛውን እያጠፋን የኛ ላልሆነው ነገር ስንሟሟት ስንደክም ስንጣጣር ስንታትር እንዳንገኝ ግን እጅጉን ልንጠነቀቅ ይገባል፡፡ የምንቀበርበት የምድሪቱ አፈር አይቀበለንም፡፡ ታሪክና ማንነት ይታዘቡናል፡፡

ማንም እንደ ሮቦት (ተንቀሳቃሽ ማሳልጥ) እንደፈለገ በፈለገው መንገድ የሚነዳን ያዘዘንን የምንፈጽም ለምን? የሚባል ነገር የማናውቅ እቃ መሆን የለብንም፡፡ እኛ ኢትዮጵያዊያን የራሳችን የሆነ ማንነት፣ ታሪክ፣ ባሕል፣ መለያ፣ ፍላጎት፣ ጥቅም ወ.ዘ.ተ ያለን የተሟላ ሰብእና ባለቤት የሆንን ሕዝብ ነንና፡፡ እንዴ! እኛ እኮ ታላቅ ሕዝብ ነን፤ እኛ እኮ መሠረት ነን፤ እኛ እኮ በጥንታዊቷ ግሪክ ፈላስፎች ጸሐፍትና ሕዝብ ዘንድ ከአማልክቶቻቸው ጋር እኩል ደረጃ ክብር ልዕልና እንዳለን ይቆጥሩን የነበርን ድንቅ ሕዝብ ነን፡፡ ይሄና ሌሎችም ስለኛ ክብር ታላቅነት ልዕልና የሚነገሩ ብርቅና ድንቅ መገለጫዎች እንዲሁ ዝም ተብሎ ያለምንም ምክንያትና መነሻ የሚፈጠር ወይም የተፈጠረ ስም ይመስላቹሀልን? ከእባካቹህ እኛ እንዴት በማይረቡ በተልከሰከሱ ነገሮች  እንገመታለን? ይህን ተራ ተራውን ነገር እርሱት ከእርስ በእርስ ሽኩቻ ራቁ፡፡ የነበረውን ታላቅነታቹህን ፈለጉ! ምን እንዳጠፋው መርምሩ! ከዚያም ተማሩ! ለመመለስም እንቅልፍ ሳያምረን እንልፋ! እንጣር! እንታትር!

እራሱን፣ ታሪኩን፣ ማንነቱን፣ የማያውቅና ሲነግሩትም የማያምን ተረት ተረት የሚመስለው ወኔው የተሰለበ ትውልድ አካል መሆናችን እጅግ ያሳዝናል፡፡ %ረ እባካቹህ እኛ እኮ ታውቃላቹህ? ምን ያህል?… እንዴት ከዛ ከመጠቀ ከረቀቀ ሉዓላዊ የአስተሳሰብና የሰብእና ምጥቀት፣ ርቀት፣ ደረጃ ወርደን ተንሸራተን በማይረባ በሚረባ ተራው ነገር ሁሉ እርስ በርስ በመናቆር በመሻኮት የወጣችውን ጀንበር በከንቱ የምንሸኝ የሸረኞችና የክፉዎች መዝናኛ መሳቂያና መሳለቂያ በመሆን ከንቱ ማኅበረሰብ ሆነን እንቅር? እርግጠኞች ናቹህ ይጠቅመናል? ይህ ያለንበት አዋራጅ አሸማቃቂ የድህነት አረንቋ በቂ መልስ አይሰጥም? ሌላ ተጨማሪ የሚባክን ጊዜ ያስፈልገናል? ሌላ ድቀት ሥብራት መሸከም የሚችል አቅም ጉልበት ትክሻ አለን? %ረ ተው? ለምን እራሳችንን የቁማረተኞች የተበላ ካርድ እናደርጋለን?

ወደ ቀደመው ነገራችን ስንመለስ ኢሕአዴግ አንበሳውን ከሰንደቁ ካስወገደ በኋላ ያልተለመደና ከቅርሶቻችን ወይም ከማንነታችን ጋር ግንኙነት የሌለውን ኮከብ ለጥፎ ከአንድ ዐሥተ ዓመታት ላለፈ ጊዜ ከቆዬ በኋላ ከቀደሙት መንግሥታት በተለየና ባልተለመደ መልኩ ቀደምቱን ማለትም ሌጣውን ዓርማ ያለበትን የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ መጠቀም የሚከለክል፣ በሰንደቅ ዓላማው ላይም የኢፌድሪን ዓርማ እንዲሰፍርበት የሚያስገድድ፣ ይሄንን የማያደርገውን የሚቀጣ እና ሌሎችም በአዋጁ መውጣቱ ግርምትን የሚፈጥሩና ሰንደቁን ከሕዝቡ ሕዝቡን ከሰንደቁ የሚያራርቁ ለመቀበልና ለመተግበር ከቶውንም የማይቻሉና የማይገቡ አንቀጾችን ጨምሮ ሥራ ላይ እንዲውል አጸደቀ፡፡

ሲመስለኝ እንደሚታወቀው ኢሕአዴግ ሥልጣን እንደያዘ ከዚያም በፊት የኢትዮጵያን ሰንደቅዓላማ የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ አድርጎ ለመቀበል እጅግ ተቸግሮ እንደነበርና በትጥቅ ትግል እያለም ሰንደቋን የበሶ የስኳር የዱቄትና የዕቃ መያዣ አድርገው ይገለገሉበት እንደነበረ ከታሪካቸው ወይም ከነባር ታጋዮቻቸው ይፋ የወጡ መረጃዎች ያረጋግጣሉ፡፡ ሥልጣን ከያዘ በኋላም ጭራሽም እንደአዲስ ሀገር ሁሉ ሰንደቅ ዓላማው ምን ዓይነት ይሁን? ብሎ ጉዳዩን ለውይይት አቅርቦት እንደነበር ይታወሳል፡፡ ነገር ግን ከብዙ አቅጣጫዎች አንፃር አዲስ ሰንደቅዓላማ መጠቀም የማይቻል መሆኑን ሲረዳ ጨርቅና ከሌላም የንቀት ቃላት መቅድም ጋር የራሱን ምልክት እላይዋ ላይ እንዲሠፍር በማድረግ ሰንደቋን ለመቀበል ተገደደ፡፡

ጨርቅ መሆኑ መቸ ጠፋን?፣ ጨርቅ መሆኗንስ የማያውቅ ማን ይኖራል? አፉን ከፈታ ሕፃን ጀምሮ የሰንደቅዓላማን ጨርቅነት ሊናገር የማይችል ሰው ይኖራል እንዴ? ነው ወይስ ሰውየው የሰንደቅ ዓላማን ምንነትና ትርጉም ሲመረምሩ የሚያውቁት ነገር ከጨርቅነት ያለፈ ነገር ስለሌለ? ሰብእናቸውም ሰንደቃችን ማንን እንደምትወክል ለመረዳት ለመገንዘብ የማይፈቅድላቸው ሆኖ?

እናም አዋጁን አጸደቀ ይሄኔ ሰንደቁ ንዋዬ ቅድሳቷ ለዚያውም የመጀመሪያው የሆነው ቤተክርስቲያን ችግር ገጠማት፡፡ ተቆርቋሪ ጳጳሳትም ሳይቀሩ ፈራ ተባ እያሉ ቤተክርስቲያን ሌጣውን ዓርማ አልባውን ሰንደቅ የምትይዝበትን ሃይማኖታዊ ምክንያት ቀርበው አስረዱ፡፡ ይሄንን ግንዛቤ ውስጥ በማስገባትም ይመስላል ይህንን አዋጅ ከማርቀቅ እስከ ማጽደቅ ድረስ ኃላፊነቱን ወስዶ ይሠራ የነበረው የአገዛዙ አካል አንድ ኃላፊም አዋጁ ቤተክርስቲያንን እንደማይመለከት ማለትም ቤተክርስቲያን እምነቷ በሚያዛት መሠረት ሌጣውን ወይም ከንዋዬ ቅድሳቶቿ አንዱ የሆነውን ሰንደቅ እንድትጠቀም መፈቀዱን በብዙኃን መገናኛ ገለጹ፡፡

ከአዋጁ በኋላ ግን ይህንን ቃል በሚቀለብስና ግራ በሚያጋባ ሁኔታ በሚያስደንቅ ፍጥነት የቤተክርስቲያን የቃል ኪዳን ምልክቶች ወይም ሰንደቅ ንዋዬ ቅድሳቶቿ (ትእምርተ-ኪዳናቷ) ላይ ያለአንዳች ፈሪሐ እግዚአብሔር በአረማዊ ድፍረት ቤተክርስቲያን ውስጥ ያሉ የቤተክርስቲንን እንጀራ የሚበሉ ካህናት ነን ባዮች ነገር ግን እጅግ በሚያሳዝን ሁኔታ የእግዚአብሔር ሳይሆኑ የሌላ አካል አገልጋዮችና ጉዳይ ፈጻሚዎች በሆኑ ግለሰቦች እነዚያ ንዋዬ ቅድሳት እላያቸው ላይ ለዚያውም በቤተክርስቲያን ወጪ ቀለም ተገዝቶ እየተለቀለቁ ባለ ኮከብ ዓርማ ለማድረግ ተሞከረ፡፡ ነገር ግን ቀለም በመቀባት ሊያሠፍሩት የሚፈልጉት ኮከብ በሚፈልጉት ጥራት ባለመውጣቱ ከመንግሥት አካላት ጋር በመቀናጀት የየቤተክርስቲያኑን ትእምርተ ኪዳናት (ሰንደቅ) አንድ ሳያስቀሩ ለቅመው በመውሰድ በምትኩ ኮከብ ያለበትን አምጥተው ቤተክርስቲያናቱን አጥለቀለቁት፡፡ ሁኔታው አእምሯቸውን ያወከው አንዳንድ ካህናት ድርጊቱ ፈጽሞ ትክክል አለመሆኑን ለማስረዳት ሲሞክሩ ሲቃወሙና ለመከላከል ሲሞክሩም ለእንግልትና ለአስተዳደራዊ ቅጣት ተዳረጉ፡፡

በዚህም ምክንያት ከዚህ በኋላ በተለይ በአዲስ አበባ አብያተክርስቲያናት ውስጥ በቤተክርስቲያን ክብረ በዓላት ላይ የመጀመሪያዋን ንዋዬ ቅድሳቷን (የቃል ኪዳን ምልክቷን) ሰንደቅ ለምልክት እንኳ አንድ ማየት የማይቻል ሆኖ ቁጭ አለ፡፡ ነገር ግን ጎንደር እስከማውቀውቀው ድረስም አክሱም ሌሎች አንዳንድ ቦታዎችም ያሉ አባቶች ከመንጋ እረኛ በሚጠበቅ በያዙት የጸና አቋም ንዋዬ ቅድሳታቸውን ፈጽሞ ሳያስደፍሩ ጠብቀው ይዘዋል፡፡ በክብረ በዓላቶችም ለምሳሌ በጥምቀት በመስቀልና በንግሥ አንድ እንኳን ሌላ ሳይቀላቅሉ በሚያስደስት ሁኔታ የቃል ኪዳኑን ምልክት ብቻ ይዘው በመውጣት እግዚአብሔርን ያከብሩበታል፡፡

ለእነዚህ ጸያፍ ድፍረት ለፈጸሙት ስመ ካህናትም ካድሬዎች በየበረሀው፣ በየዋሻው፣ በየገዳሙ ያሉ ቅዱሳን አባቶች ከእግዚአብሔር የተነገረንና የታዘዝነው ነው ያሉትን መልእክትና ከባድ ተግሳጽ ላኩ መልእክቱም “ወዮላቹህ! እናንት የእፉኝት ልጆች ስመ ካህናት ወዮላቹህ! የአፍኒንና ፊንሐስ እጣ ፋንታ ይጠብቃቹሀል፡፡ ንዋዬ ቅድሳቴን አረከሳቹህት፣ ሕዝቤን ለአሕዛብ ጣዖት አሰገዳቹህት ወዮላቹህ ወዮታ አለባቹህ” የሚልና በተሎ ንስሐ እንዲገቡ የሚያስጠነቅቁ መልእክቶች ከየ አቅጣጫው ተነገረ፡፡ ለአሕዛብ ጣዖት መባሉ እንደሚታወቀው ቅዱሳት መጽሕፍትና ታሪክ እንደዘገቡት በፀሐይ በጨረቃ በከዋከብት በሌሎችም ፍጥረቶች እንደሚያመልኩትና ለእነሱም እንደሚሰግዱት ፈጣሪን እንደማያውቁት ማለቱ ነው፡፡

ከእነዚህ ውስጥ ዛሬ ክርስትናን ተቀብለናል የሚሉ ሀገራትም ይገኙበታል በዚያ ጊዜ ለእነዚያ አማልክቶቻቸው የሠየሟቸው የቀናት ሥያሜዎች ዛሬም ድረስ አሉ፡፡ ሁሉም የቀናትና የወራት ሥያሜዎቻቸው በአማልክቶቻቸው ስም የተሠየሙ ናቸው፡፡ ለምሳሌ Sunday (የፀሐይ አምላክ ቀን) Monday, Moon day (የጨረቃ አምላክ ቀን) ሁሉም የሳምንቱ ቀናትና የወራት ሥያሜም ጭምር ናቸው፡፡ አሰገዳቹህት ማለቱም በቤተክርስቲያኗ ቀኖና መሠረት ከሦስቱ የስግደት ዓይነቶች ሁለተኛውን ለንዋዬ ቅድሳትና ለቅዱሳን ባጠቃላይ የእግዚአብሔር ጸጋ ላደረበት ሁሉ ስለ ጸጋው ባለቤት ስለ ፈጣሪ ቸርነትና ለእነሱም የሚገባቸውን ክብር ለመስጠት የሚሰገድላቸውን “የጸጋ ስግደት” ማለቱ ነው፡፡ አንደኛው ስግደት ማለትም “የአምልኮ ስግደት” ግን ለእግዚአብሔር ብቻ የሚሰገድ የስግደት ዓይነት ነው፡፡ ሦስተኛውና የመጨረሻው የስግደት ዓይነት ደግሞ “የአክብሮት ስግደት” ለነገሥታት፣ ለመሪዎች፣ ለተከበሩ ሰዎች፣ አንዳችን ለሌላኛችን ለሰላምታ በማጎንበስም በመንበርከክም እንደየዘመኑ የሰላምታ ዓይነት የምንሰግደው የስግደት ዓይነት ነው፡፡

ነገር ግን ያ ከቅዱሳኑ የተላከው መልእክት ያንን ስሕተት የፈጸሙትን ሰዎች ሊያስደነግጥና  ስሕተታቸውንም እንዲያርሙ ሳያደርጋቸው ቀረ፡፡ እንዲውም ጭራሽ እንደዚህ እያሉ ይናገሩ የነበሩትን አባቶችና እናቶች ለማሳሰር ተሯሯጡ አሳሰሩም፡፡ ከዚያም በኋላ ሌላው ቀርቶ በቦታው ኖሬ በዓይኔ እንዳየሁት መስቀል አደባባይ ለመስቀል በዓል አከባበር ትእምርተ ኪዳኑ (የቃልኪዳን ምልክቱ) ያለበትን ጥንግ ድርብና ጃኖ ያደረጉትን ካህናትና የሰንበት ተማሪዎች ጥንድ ድርባቸውንና ጃኗቸውን ገፈው ሲወስዷቸው ተመልክቻለሁ፡፡ ብቻ በዚያም በዚህም ብለው በመረባረብ በተለይ በአዲስ አበባ በሚገኙ አብያተክርስቲያናት የቃል ኪዳኑን ምልክት ከነአካቴው አጠፉት፡፡ ከሊቃነ ጳጳሳት በዚህ ድርጊት እጅግ ያዘኑ ቢኖሩም በተወሳሰበ ሸር ምክንያት በቅዱስ ሲኖዶስ ደረጃ ተወያይተው አቋም እንዲያዝ ማድረግና የቤተክርስቲያኗን ጥቅም ማስጠበቅ ሳይችሉ ቀሩ፡፡ በግላቸውም ቢሆን እንደሚጠበቅባቸው ሁሉ የጸና አቋም በመያዝ ሊሟገቱና ሊከላከሉ አልቻሉም፡፡ በመሆኑም ለሽዎች ዓመታት ያስቆጠረውና የመጀመሪያው ንዋዬ ቅድሳት ህልውና በብዙ አብያተክርስቲያናት ውስጥ ሊጠፋ ችሏል፡፡

እኔ ግን አንድ ግራ የሚገባኝ ነገር አለ ይሄንን ያደረጉ ካህናት ካህንነቱ ቀርቶ እንዲያው በእግዚአብሔር መኖር እንኳ የሚያምኑ ሰዎች ናቸውን? ቢያምኑ ኖሮ በዚህ ደረጃ ይንቁትና ይዳፈሩት ነበርን? ነገ በማይቀርላቸው ሞት ሲወሰዱ ከፊቱ ቀርበው የሚገጥማቸው ፍርድ ትንሽም እንኳ አያሳስባቸውም ነበርን? እኔ በምንም ተአምር በእግዚአብሔር የሚያምን ሰው ፈጣሪን እንደሚያስከፋ እያወቀ ይሄንን ድፍረት ይፈጽማል ብየ ለማመን እጅግ እቸገራለሁ፡፡ ነገር ግን የሚያገለግሉትን አካል ለማገልገልና የግል ኑሯቸውንም ለመኖር ያመቻቸው ዘንድ በካህን ስም ገቡ እንጅ ካህናት እንኳን አይደሉም፡፡ እነዚህን ሰዎች በዚህ ብቻ ሳይሆን በሌሎችም በብዙ ነገሮች እንደታዘብኳቸው ሃይማኖት የሚባል ከቶውንም የላቸውም፡፡ አላቸው ከተባለ ሃይማኖታቸው እንትንነት አምላካቸውም አቶ እንትና ነው፡፡ ከዚህ ውጭ ምንም የሚያውቁት ነገር የለም እንዲኖርም አይፈልጉም አይፈቅዱምም፡፡

ጽሑፌን ከመቋጨቴ በፊት ለሁለት አካላት መልእክቴን ማስተላለፍ እወዳለሁ፡፡ አንደኛው “እራሱን መንግሥት ብሎ ለሚጠራው ቡድን” ሲሆን መልክቴም “መንግሥት በሃይማኖት ጉዳይ ጣልቃ አይገባም” የሚል ድንጋጌ የራሱ ሕገ መንግሥት ደንግጓል፡፡ በተግባር እየሆነ እንደምናየው ግን ያልገባበት የሃይማኖት ጉዳይ አለመኖሩን ነው፡፡ ቤተክርስቲያን ከንዋዬ ቅድሳቷ አንሥቶ አስከ በዓላቶቿ ድረስ ባልተረዱት ነገር ላይ ፈጽሞ የተሳሳተ ትርጉም ተሰጥቶት ሃይማኖታዊ አስተምህሮዋን ማስጠበቅ፣ ማስከበር፣ ማራመድ፣ ማስተማር እንዳትችልና እነኝህን እሴቶቿን እንድታጣ ተደርጓል፡፡ በመሆኑም የገዛ ሕገመንግሥቱ ለደነገገው አንቀጽ ታማኝ በመሆን ያ የሰንደቅ ዓላማ አዋጅ ቤተክርስቲያንን  እንደማይመለከት በግልጽና በተግባርም እንዲያረጋግጥ፣ ግለሰቦችም በሌሎች ንዋዬ ቅድሳት እንደሚገለገሉ ሁሉ በትእምርተ ኪዳኑም የመገልገል መብታቸውን እንዲያከብር፣ ያንን ስሕተት በቤተክርስቲያን ላይ የፈጸሙትን ግለሰቦችና ቡድኖች እያደረጉት ያለው ነገር ከእሱ ፍላጎት ውጭ ከሆነ ይሄንን በግልጽ እንዲረዱና ስሕተታቸውን እንዲያርሙ እንዲያደርግ የሚለው ሲሆን፡፡

ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው
ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው

ሁለተኛው መልእክቴ ደግሞ ለኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን “ቅዱስ ሲኖዶስ ተብየ” ነው መልእክቴም እንደሚታወቀው የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ተግባር ቃሉ እንደሚለው “በገዛ ደሙ የዋጃትን የእግዚአብሔርን ቤተክርስቲያን ትጠብቋት ዘንድ መንፈስ ቅዱስ እናንተን ጳጳሳት አድርጎ ለሾመባት ለመንጋው ሁሉ እና ለራሳቹህ ተጠንቀቁ ከሄድኩ በኋላ ለመንጋው የማይራሩ ጨካኞች ተኩላዎች እንዲገቡባችሁ ደቀመዛሙርትንም ወደኋላቸው ይስቡ ዘንድ ጠማማ ነገርን የሚናገሩ ሰዎች በመካከላቹህ እንዲነሡ እኔ አውቃለሁ” ሐዋ. ሥራ 20÷28-31 እንደሚለው ነውና ቤተክርስቲያን ለሚገጥሟት ችግሮች ሁሉ የቤተክርስቲያንን ጥቅም በሚያስጠብቅ መልኩ ተግቶ መሥራት ሆኖ እያለ ይሄንንና ሌሎችም ቤተክርስቲያን የገጠሟትን ፈተናዎች ዓይቶ እንዳላየ ሰምቶ እንዳልሰማ ከማለፍም አልፎ ተባባሪ እየሆነም ነው፡፡ ይሄም ፍጹም የለየለት ክህደት ነው፡፡ በመሆኑም ይህ የሆነበትን ምክንያት መርምሮ በሁኔታው እጅግ አዝኖና ተጎድቶ ላለው ለሕዝበ ክርስቲያኑ እንዲገልጽ የማስተካከያ እርምጃም እንዲወሰድ በማድረግም ለቤተክርስቲያኗ ያለውን ኃላፊነት እንዲወጣ ህልውናውንና የተጣለበትን አምላካዊ አደራም በመጠበቅ እንዲያረጋግጥ የሚለውን የሕዝበ ክርስቲያኑን ኃዘን ፍላጎትና ምኞት ማስተላለፍ እወዳለሁ፡፡

ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር!!!

amsalugkidan@gmail.com

Check Also

አማራና ትግሬ ተስማሙና ኦሮሙማን መክቱ። – ሞጣ ቀራንዮ

https://fb.watch/f-ipLpwPrZ/ Related Posts:አማራና ኦሮሞ አትጣሉ። ተዋደዱ !አማራና ትግሬ ወደ አዲስ አበባ እንዳይገቡ የኦሮሞ ክልል አስተዳደር …

ማስጠንቀቂያ ለከንቲባ አዳነች እቤቤ!

Related Posts:የጃዋር ሞሃመድ የዜግነት አወዛጋቢ ጉዳይ. ጃዋር ማስጠንቀቂያ ተሰጠው !

Multi threaded Redundant Dedicated Server in USA and in Europe.