Breaking News
Home / News / ኢትዮጵያ ኢንትርኔትን ስታቋርጥ በየቀኑ 4.5 ሚሊዮን ዶላር ታጣለች::

ኢትዮጵያ ኢንትርኔትን ስታቋርጥ በየቀኑ 4.5 ሚሊዮን ዶላር ታጣለች::

ኢትዮጵያ የኢንተርኔት አገልግሎትን በምታቋርጥባቸው እያንዳንዱ ቀናት በትንሹ ከአራት ሚሊዮን ዶላር በላይ እንደምታጣ የኢንተርኔት ነጻነትና ተደራሽነትን የሚቆጣጠረው ኔትብሎክስ የተባለው ድርጅት ዳይሬክተር ለቢቢሲ ገለጹ።

ዳይሬክተሩ እንዳሉት “ኢትዮጵያ ኢንትርኔትን ለአንድ ቀን ስታቋርጥ ከገቢ አንጻር ቢያንስ 4.5 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ታጣለች።” ይህም ሌሎች ኪሳራዎችን ሳይጨምር የሚከሰት ጉዳት ሲሆን በተጨማሪ ደግሞ ለኢኮኖሚያዊ እድገት ወሳኝ የሆኑት የመዋዕለ ነዋይ አፍሳሾች ዘንድ እምነት ማጣትን ያስከትላል።

ከሁለት ዓመታት በፊት ኢትዮጵያ በኢንትርኔት መቋረጥ ሳቢያ በቀን 500 ሺህ ዶላር ታጣ የነበረ ሲሆን በአሁኑ ወቅት በኢንተርኔት የሚንቀሳቀሰው የኢኮኖሚ ክፍል እየሰፋ በመሆኑ የኪሳራው መጠን ከፍ እንዲል እንዳደረገው ይታመናል።

የኢንተርኔት አገልግሎትን የተለያዩ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች በዋናነት የሚጠቀሙ በመሆኑ በርካታ የአፍሪካ ሃገራት በዚሁ ቴክኖሎጂ ላይ ጥገኛ እየሆኑ እንደሆነ የኢንተርኔት ነጻነትና ተደራሽነትን የሚቆጣጠረው ኔትብሎክስ የተባለው ድርጅት ዳይሬክተር አልፕ ቶከር ተናግረዋል።

የአፍሪካ ሃገራት በግለሰብ ደረጃ የሚደረግ የገንዘብ ዝውውርን ጨምሮ ከፍ ያሉ ቁልፍ እንቅስቃሴዎችን ኢንተርኔትን በመጠቀም የሚከውኑ በመሆናቸው ኢትዮጵያን ጨምሮ የአገልግሎቱ መቋረጥ በሚከሰትባቸው ሃገራት ላይ ከፍ ያለ ኢኮኖሚያዊ ጫና እንዳለው አልፕ ይናገራሉ።

ኢትዮጵያ ከሁለት ዓመታት በፊት በተለያዩ የሃገሪቱ ክፍሎች ተከስቶ የነበረውን ጸረ መንግሥት ተቃውሞ ለመግታትና የፈተና መሰረቅን ለመቆጣጠር ስትል ለ36 ቀናት ያህል የኢንተርኔት አገልግሎትን በማቋረጧ ከ130 ሚሊዮን ዶላር በላይ እንዳጣች የምሥራቅና ደቡባዊ አፍሪካ ዓለም አቀፍ የመረጃ ቴክኖሎጂ ፖሊሲ ትብብር የተሰኘው ተቋም አሳውቆ ነበር።

በተለያዩ የአፍሪካ ሃገራት ውስጥ የተለያዩ ችግሮች በተለይ ደግሞ ፖለቲካዊ ቀውሶች ሲያጋጥሙ መንግሥታት በቀዳሚነት የኢንተርኔት አገልግሎት በማቋረጥ ችግሮችን ለመቆጣጠር ጥረት ያደርጋሉ።

• ኢትዮጵያ ኢንተርኔትን በመዝጋቷ ከ130 ሚሊዮን ዶላር በላይ አጣች

ከሁለት ዓመት በፊት ጀምሮ ኢትዮጵያ ኢንተርኔትን በመዝጋት ከሚታወቁ የአፍሪካ ሃገራት መካከል አንዷ ለመሆን ችላለች። የኢትዮጵያ መንግሥት ለውጥ እንዲያደርግ ያስገደደው ሕዝባዊ ተቃውሞ ካበቃ በኋላ ሆን ተብሎ የተደረገ ሃገር አቀፍ የኢንተርኔት መቋረጥ አላጋጠመም ነበር።

በዚህ ሳምንት ግን ሃገር አቀፉ ፈተና ከተጀመረ ከአንድ ቀን በኋላ የኢንትርኔት አገልግሎት በመላው ሃገሪቱ ተቋርጧል። ብልጭ ድርግም እያለ ቆይቶ ባለፉት ሁለት ቀናት ሙሉ ለሙሉ ተቋርጧል።

ይህንን በተመለከተም ብቸኛው የቴሌኮም አገልግሎት አቅራቢው መንግሥታዊው ኢትዮቴሌኮምም ሆነ ሌላ የሚመለከተው የመንግሥት አካል የኢንተርኔት አገልግሎት የተቋረጠበትን ምክንያት በይፋ ለመናገር አልደፈሩም። አሁንም ድረስ ለአገልግሎቱ መቋረጥ በርካቶች የሚጠቅሱት ሀገር አቀፉን ፈተና ነው።

ተጠቃሚዎች ኢንተርኔት በመቋረጡ ምን ገጠማቸው?

ቀነኒ ሂኮ በአሰላ ዩኒቨርስቲ የሁለተኛ ዓመት የፋርማሲ ተማሪ ነች። በዩኒቨርስቲ ውስጥ ትምህርት ነክ መረጃዎችን ለመለዋወጥ ያስችላለቸው ዘንድ የትምህርት ክፍሏ ተማሪዎች የቴሌግራም ቡድን አቋቁመው ነበር። በዚህ ቡድን መምህሩ ክፍለ ጊዜ ቢሰርዝ፣ የቤት ሥራ ቢሰጥ ወይንም የተከታታይ ምዘና መምህሩ ቢያቅድ መልእክት ይለዋወጡበታል።

አሁን ግን የኢንተርኔት አገልግሎቱ ስለተቋረጠ ምንም ዓይነት መረጃ መለዋወጥ አልቻሉም። ይህ በጅማ ዩኒቨርስቲ ተማሪ ለሆነው መሐመድ ቃሲምም ተመሳሳይ ነው። የመማር ማስተማሩን ሂደት ያለ ያለኢንትርኔት አገልግሎት ማሰብ ከብዶታል።

መረጃ ለመለዋወጥ፣ የተለያዩ የሚሰጡ ሙከራዎችን ለመስራትና በአጠቃላይ ከኢንተርኔት መኖር የሚያገኛችው ጥቅሞች፣ መፅሀፍት ከኢንተርኔት ለማግኘት እንዲሁም የሌክቸር ቪዲዮዎችን ማየት ስላልቻለ ከእለት እቅዱና ትምህርቱ መደናቀፉን ይናገራል።

ቀነኒም አክላ በመምህራንና በተማሪዎች መካከል የነበረው ግንኙነት ስለተቋረጠ መቸገራቸውን ትናገራለች። በኢንተርኔት እና የሞባይል አጭር መልዕክት መቋረጥ በባንኮች ላይ ያደሳደረውን ተፅዕኖ ለመጠየቅ የደወልንባቸው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ የኦሮሚያና የዳሸን ባንኮች ስልኮች ባለመስራታቸው ምላሽ ማግኘት አልቻልንም።

የአቢሲኒያ ባንክ የማርኬቲንግ፣ የኮሙኑኬሽንና ኦፕሬሽን ሥራ አስኪያጅ የሆኑት አቶ አስቻለው ታምሩ የኢንተርኔት መቋረጡ የእኛ አገልግሎት ላይ ያሳደረው ተፅዕኖ የለም ሲሉ ነግረውናል።

“ኢንተርኔቱን በተመለከተ ባንኩ የሚጠቀምበት ቲ24 የተባለ የተለየ የኢንተርኔት መስመር ስላለ እርሱ በአግባቡ እየሰራልን ነው” ብለዋል።

ነገር ግን ከባህር ማዶ ገንዘብ ለሚላክላቸው ሰዎች ገንዘቡን በባንካቸው ቅርንጫፍ እንደገባ የሞባይል አጭር መልዕክት የእጣ ቁጥር ይልኩ እንደነበር ያስረዳሉ። አሁን ግን ይህንን ማድረግ ተቸግረናል በማለት የሞባይል የአችር መልዕክት ባለመስራቱ መቸገራቸውን ነግረውናል።

Check Also

የፓርላማ ተወካዮች ፀረ አማራ የሆኑ ዝርዝር ከነስልክ ቁጥራቸው

Related Posts:የህዝብ ተወካዮች ስልክ ቁጥር ዝርዝር።ይሄ ፀረ ኢትዮጵያ የሆነው ሀንጋሳ ኢብራህም የሚባለው ኦህዴድን ብልጥግናን ወክሎ …

የህዝብ ተወካዮች ስልክ ቁጥር ዝርዝር።

ሼር ይደረግ! የህዝብ ተወካዮች የምክር ቤት በነገው እለት በአማራ ህዝብ ላይ ያወጀውን የእልቂት አዋጅ ለማፅደቅ …

Multi threaded Redundant Dedicated Server in USA and in Europe.