Breaking News
Home / Amharic / ቤተክርስቲያኒቱ ከባለፈው የበለጠ ብርቱ ፈተና እየመጣባት ነው። መሳይ መኮነን

ቤተክርስቲያኒቱ ከባለፈው የበለጠ ብርቱ ፈተና እየመጣባት ነው። መሳይ መኮነን

ቤተክርስቲያኒቱ ከባለፈው የበለጠ ብርቱ ፈተና እየመጣባት ነው።
እነአብይ አሁን ብቻቸውን አይደሉም። ከእነጌታቸው ረዳ ጋር ተጣምረው ለቤተ ክርስቲያኒቱ የማያባራ ቀውስ ይዘውላት እየመጡ ነው። እንግዲህ ቆዳን ወፈር አድርጎ የሚገባበት ግዙፍ አደጋ ከፊታችን ተደቅኗል። እንደሚሰማው በይቅርታ ገቡ የተባሉት ሶስቱ አባቶች የተሰጣቸውን ልዩ ተልዕኮ ሲያከናውኑ ቆይተዋል። ወደ ትግራይ በማቅናት እዚያ ካሉና አፈንግጠው ከተቀመጡ አባቶች ጋር ምክክር አድርገዋል። የኦሮሚያ ብልጽግናና ህወሀት ከፖለቲካው ባሻገር በሃይማኖትም ጋብቻ ሊፈጽሙ ተስማምተዋል። ለቤተክርስቲያኒቱ ይህኛው ትንሽ ጠንከር ያለ ነው። ባለፈው የህዝብ ማዕበል አስደንግጧቸው ጂናቸውን ወደ ብልቃጧ መልሰው የከተቱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ”የመጨረሻ” የተባለውን በቤተክርስቲያኒቱ ላይ የታሰበውን እቅድ ወደ ተግባር ለመለወጥ ሸሚዛቸውን ወደላይ እየጠቀለሉ ነው። የግንቦቱ የሲኖዶሱ ጉባዔ ለቤተክርስቲያኒቱ አባቶች በጎልያዶች በእጅጉን የሚፈተኑበት እንደሚሆን ከወዲሁ ፍንጮች በስፋት እየታዩ ነው።…ግንቦት 24 የቀን መቁጠሪያችሁ ላይ ምልክት አድርጉ።

ከወዲያ ሰሜን ሸዋ አጣዬ ዙሪያ፡ ማጀቴና አከባቢው የአብይ ሰራዊት የጭካኔ በትሩን ከምንጊዜውም በላይ እያሳረፈ ነው። የእምነት ቦታዎች አልቀሩም። የአርሶ አደሮች መኖሪያ ቤቶች እንደካልሲ እየተገለበጡ እየተበረበሩ ነው። በእርሻ ማሳቸው ላይ ያሉ ገበሬዎች ሞፈርና ቀንበር እንደያዙ ተደብድበዋል። ህጻናት ተንገላተዋል። ፋኖዎችን አምጣችሁ ውለዱ፡ ደብቃችኋል በሚል መከራ ስቃዩን እየተጋቱት ነው። ዲሞፍተር ለያዘ የአከባቢው ነዋሪ ብረት ለበስ ሰራዊት ተመድቦለታል። ኔትወርክ የለም። ስልክ በመከራ ካልሆነ አይገኝም። የኦሮሚያ ብልጽግና አከባቢውን ከግንኙነት ውጪ አድርጎ እያተራመሰው ነው። ሰሜን ጎንደር ህዝቡ ትንሽ ስለጠነከረበት ወደኋላ አፈግፍጎ በሽማግሌ በኩል እየሞከረ ነው። ይሄ የሽማግሌ ነገር ሀገር እያጠፋ ነው። የአምባገነኖችና ጨቋኞች ድሮን ሆኗል። ሰሜን ሸዋ ህዝቡ የተዘናጋው ሽማግሌዎች ተልከውበት እንደሆነ ሰምተናል። ሰሜን ጎንደር ላይ በእርግጥ የሚሳካ አይመስልም። ህዝቡን በአውራጃና ጎጥ ከፋፍሎ ለመበታተን የተጀመረው ስውር ሴራ ስጋ ለብሶ አማራ ክልል ላይ በመንጎማለል ላይ ነው።

የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት(ሸኔ) ሀይ ባይ አጥቷል። አዲስ አበባ አፍንጫ ስር ያሻውን እያደረገ ነው። የሀዋሳና ጅቡቲ መስመሮችን በአብዛኛው ተቆጣጥሮአቸዋል። ሁለቱ የሀገሪቱ የደም ስር ናቸው የሚባሉት የየብስ ትራንስፖርት መስመሮች በኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት በሚፈጸሙ ጥቃቶች ትልቅ የስጋት ቀጠና ሆነዋል። ሰሞኑን በአፋር ክልል አንድ ባለስልጣን ላይ ጨምሮ የተፈጸሙት ግድያዎች የፌደራሉ መንግስት ወይ አቅቶታል፡ አልያም የሆነ የተቆመረ ነገር አለ እንድንል እያስገደዱን ነው። ሞት ተለምዶ ሰዉ ምንም አይመስለውም ይሉናል የምናናግራቸው የአከባቢው ነዋሪዎች። ወደ ሀዋሳ የሚወስደውና እስከሞያሌ የተዘረጋው መስመርም የታጣቂዎች መፈንጪያ ከሆነ ሰነባብቷል። በማታ ጉዞ ከሞት ጋር ቁማር የመጫወት ያህል አደገኛ ሆኗል። በነፍሱ የቆረጠ ካልሆነ በስተቀር ከምሽቱ 12 ሰዓት በኋላ በዚያ መስመር መጓዝ የማይሞከር ሆኗል። መቂ ከተማ ባልታወጀ የአስቸኳይ ጊዜ ውስጥ ሆና የሰዓት ገደብ በመጣል እንቅስቃሴዎችን አቁማለች። የምናናግራቸው ሰዎች በሸኔና በኦሮሚያ ልዩ ሃይል መሀል ልዩነቱ ጠፋብን ይላሉ። ማለያ እየቀያየሩ የሚገድሉትና የሚዘርፉት እነሱ ናቸው ሲሉም ይገልጻሉ። የሚገርመው በሁለቱም መስመሮች ግዙፍ የመከላከያ ሰራዊት ካምፖች በቅርበት መኖራቸው ነው።

የኢኮኖሚው ነገር አይነሳ። እዚያው ተከድኖ ቢቀመጥ ይሻላል። ኢትዮጵያ ተአምረኛ ሀገር፡ ህዝቡ ታጋሽ ሆኖ እንጂ አሁን ያለንበት የኢኮኖሚ ሁኔታ መንግስት የሚያስገለብጡ አያሌ አመጾችን ይቀስቅስ ነበር። መቼም ኑሮ ካሉት መቃብርም ይሞቃል የምትል እጅግ አደንዛዥ ብሂል የፈጣሪ ቃል ያህል የሚከበርባት ሀገር ስለሆነች ሰዉ ቢጭኑት አህያ፡ ቢሎጉሙት ፈረስ መሆኑን ገዢዎቹም ተረድተው እንደፈለጋቸው ይቀልዱበታል። አሁን ያለው የግሽበት መጠን ከዓለም አደገኛ ግሽበት ያለባቸው 10 ሀገራት ግንባር ቀደሟ ኢትዮጵያ እንደሆነች ያመላክታል። በአፍሪካ አማካኙ የግሽበት መጠን ከ4 እስከ 8 በመቶ ሲሆን ኢትዮጵያ ላይ ያለው 38 በመቶ ደርሷል። በሚቀጥሉት ጊዜያት አንድ ኪሎ ቲማቲም ለመግዛት ገንዘብ በቦርሳ ሳይሆን በጆንያ ጭኖ ገበያ የሚወጣበት እንደሚሆን መግለጹ ሟርተኛ እንዳያስብል እሰጋለሁ። በአገልግሎት መስጪያ ፕሮጀክቶች ላይ ገንዘቡንና ጊዜውን እያባከነ ያለው የአብይ የ’ባዛር’ መንግስት ባዶ ሆዳችሁን፡ አንጀታችሁ በረሃብ እየተላወሰ፡ መናፈሻ ፓርክ መጥታችሁ ተዝናኑ ማለቱን ተያይዞታል። ከአፍ የሚለቅሙ የሰው ዶሮዎችን የሰበሰበው ብልጽግና ጠቅላይ ሚኒስትሩን ”የእኛ ልጅ አበጀህ፥ እሰየው” በሚል ጭብጨባና እልልታ ሀገሪቱንም ይዞ ወደገደል ተንደርድሮ እንዲገባ እያደረጉት ናቸው። ሀገር ቀውስ ውስጥ ናት ጎበዝ!
 
አቶ አያልቅበት ጣጣም የላቸውም። ህዝብን በጅምላ እየወቀሱ፡ የምመራው ህዝብ አጣሁ ዓይነት እሮሮ በአንድ ጎን እያሰሙ፡ በሌላ መድረክ ደግሞ ”ኢትዮጵያውያን የሚያበልጽጋቸው እንጂ የሚያጣላቸው ምንም ምክንያት የለም” ብለው ይናገራሉ። የእሳቸው ስሜት በበረደና በጋለ ቁጥር ሀገሪቱም ከፍና ዝቅ እያለች፡ ከመከራ ወደ መከራ እየተሸጋገረች፡ አንዱን ቀውስ ሳትገላገለው ሌላ ቀውስ እየተደረበባት እንዳቃሰተች አንድ ቀን እንደጸጉራሙ በግ አለች ስንል ድንገት ግንድስ ብላ እንዳትወድቅብን የሚል ፍርሃት ውስጤን መናጥ ከጀመረ ከራርሟል። እንግዲህ ለማይቀረው ፈተና መዘጋጀት ይገባናል። የሚመጣው ትንሽ ይከብዳል። አውቆና ተዘጋጅቶ መጠበቅ ፈተናው ብዙም እንዳይከብደን ያደርገናል።
Mesay Mekonnen. share.
 

Check Also

በአሜሪካን ሀገር የምትኖሩ የአማራ ማህበራትና የአማራ ልጆች የት ነው ያላችሁት?? Share!

ድሮን ሲያስተኩስ የነበረው ባንዳ በፋኖ ተያዘ ! እኔን ያየህ ተቀጣ !

News in Pictures

Time in Ethiopia

Multi threaded Redundant Dedicated Server in USA and in Europe.