Breaking News
Home / Amharic / በህወሓት ላይ የተጣለው የሽብርተኝነት ፍረጃ መነሳት

በህወሓት ላይ የተጣለው የሽብርተኝነት ፍረጃ መነሳት

በህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) ላይ ተጥሎ የነበረው የሽብርተኛ ቡድንነት ፍረጃ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲነሳ መደረጉን ኢዜማ እና አብን ተቃወሙ።

ረቡዕ መጋቢት 13/2015 ዓ.ም. በሚኒስትሮች ምክር ቤት በኩል ህወሓት ከሽብር ቡድኖች ዝርዝር ውስጥ ስሙ እንዲወጣ የቀረበውን ውሳኔ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአብላጫ ድምጽ አጽድቆታል።

ይህንንም ውሳኔ በመንግሥት ውስጥ ተሳታፊ የሆኑት ተቃዋሚዎቹ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ) እና የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ባወጡት መግለጫ አጥብቀው ተቃውመውታል።

ህወሓትን ከሽብርተኝነት መሰረዝ ዘላቂ ሰላምን የሚያመጣ አይደለም ያለው ኢዜማ፣ የውሳኔ ጊዜውን የጠበቀ እና ትክክለኛ አይደለም በማለት ተቃወሞውን ገልጿል።

አብን በበኩሉ ውሳኔው በተላለፈበት ዕለት በርካታ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ያልተገኙበት እና ከ60 በላይ ተቃውሞ በተመዘገበበት ሁኔታ የተላለፈው ውሳኔን የማይደግፈው መሆኑን እና ከሕጋዊነት አንጻርም ተቀባይነት እንዳይኖረው ያደርጋል ብሏል።

ከ500 በላይ እንደራሴዎች በአባልነት ከያዘው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ልዩ ስብሰባው በተካሄደበት ዕለት የተገኙት 280 ናቸው። በዚህም ህወሓት ላይ ተላልፎ የነበረውን የሽብርተኝነት ስያሜን በአብላጫ ድምጽ እንዲነሳ ሲወስን፣ 61 ተቃውሞ እና አምስት ድምጸ ታዕቅቦ ተመዝግቧል።

ሁለቱ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ባለፈው ምርጫ ተሳትፈው ጥቂት የምክር ቤት መቀመጫዎችን ያገኙ ሲሆን፣ አንዳንድ አባሎቻውም በፌደራል እና በክልል ደረጃ ኃላፊነት ይዘው እያገለገሉ እንደሚገኙ ይታወቃል።

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያሉ አባሎቻቸውም በልዩ ስብሰባው ላይ የህወሓትን ከአሸባሪነት መዝገብ መነሳትን በተመለከተ ተቃውመው አቋማቸውን አንጸባርቀዋል።

ኢዜማ እና አብን በተናጠል ባወጡት የተቃውሞ መግለጫ ላይ እንዳሉት በሰሜን ኢትዮጵያ የተካሄደውን ጦርነት ለማስቆም በመንግሥት እና በህወሓት መካከል የተፈረመው የፕሪቶሪያው ስምምነት ሙሉ ለሙሉ አለመተግበራቸውን በመጥቀስ ቡድኑን ከሽብርተኝነት ፍረጃ መውጣትን ተቃውመዋል።

ኢዜማ ትጥቅ ሙሉ በሙሉ አለመፍታቱ፣ የትግራይን የሽግግር መንግሥትን በፌደራሉ መንግሥት የበላይነት ስር አለመቋቋሙ፣ ለተፈጸሙ ጥፋቶች እና ወንጀሎች ተጠያቂነት አለመኖሩ፣ መከላከያ ሠራዊት ሙሉ ለሙሉ ትግራይን አለመቆጣጠሩ በመጥቀስ ውሳኔውን ተቃውሟል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ህወሓትን “ከሽብርተኝነት ሰርዞ ከተጠያቂነት ነፃ ማድረግ ሊቀለበስ የማይችል ጥፋት ነው” በማለት፣ በዚህም ምክንያት በህወሓት አማካኝነት “ለሚደርስ አገራዊ ጉዳት ዋነኛ ተጠያቂዎቹ ገዢው የብልጽግና ፓርቲ እና መንግሥት ይሆናሉ” ብሏል።

አብንም በበኩሉ በተመሳሳይ የሁለት ዓመቱን ጦርነት ባስቆመው የፕሪቶሪያው ስምምነት መሠረት የሚጠበቁ እርምጃዎች ሙሉ ለሙሉ ተግባራዊ ባልሆኑበት ሁኔታ ቡድኑን ከሽብርተኝነት መዝገብ መሰረዝ “ኃላፊነት የጎደለው ውሳኔ ነው” የምክር ቤቱን እርምጃ አጥብቆ ተቃውሞታል።

ጨምሮም “በመሰል አግባብነት በሌላቸው ውሳኔዎች በሕዝባችን እና አገራችን ላይ ለሚደርሰው በደል ሁሉ የፌዴራሉ መንግሥት ሙሉ ኃላፊነቱን እንደሚወስድም” አብን በመግለጫው አሳስቧል።

በትግራይ ውስጥ ጦርነት ከተቀሰቀሰ ከወራት በኋላ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሚያዝያ 28/2013 ዓ.ም. ነበር ህወሓትን ሽብርተኛ ቡድን ብሎ የሰየመው።

ረቡዕ መጋቢት 13/2015 ዓ.ም. ይህንን የሽብርተኛ ቡድንነት ውሳኔን ለማንሳት በተጠራው ልዩ ስብሰባ ላይ ፍትሕ ሚኒስትሩ ዶክተር ጌዲዮን ጢሞቲዮስ እና የጠቅላይ ሚኒስትሩ የብሔራዊ ደኅንንት አማካሪ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን በአስረጂነት ቀርበው ነበር።

የፍትሕ ሚኒስትሩ እንዳሉት ይ ውሳኔ ፕሪቶሪያ ላይ የተፈረመው የሰላም ስምምነት የትግበራ ሂደት አንድ አካል መሆኑን በመጥቀስ፣ የህወሓት ከሽብር መዝገቡ መውጣ አስፈላጊ ውሳኔዎች እየተተገበሩ “አብሮ በሂደት ውስጥ መተግበር ያለበት፤ መፈጸም ያለበት ነገር ነው” ብለዋል።

የጠቅላይ ሚኒስትሩ የብሔራዊ ደኅንነት አማካሪ አቶ ሬድዋን ሁሴንም ህወሓት ሽብርተኛ ተብሎ የተፈረጀው በሚያራምደው ርዕዮት ዓለም ወይም በፖለቲካ ፕሮግራሙ ምክንያት እንዳልሆነ ተናግረዋል።

ለውሳኔው ዋነኛ መነሻ የነበረው በወቅቱ “የህወሓትን ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ አቅሞች ለመቆጣጠር፤ በተለይም ለብሔራዊ መረጃ እና ለፌደራል ፖሊስ የተሻለ አቅም ለመስጠት ብቻ ነው” ብለዋል።

ከህወሓት በኩል የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ውሳኔን በተመለከተ በዝርዝር ያለው ነገር ባይኖርም ሊቀመንበሩ ደብረጽዮን ገ/ሚካኤል (ዶ/ር) ረቡዕ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ድርጅታቸው ከአሸባሪነት ዝርዝር ውስጥ መውጣቱ በክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ለመመስረት ጠቃሚ መሆኑን ገልጸዋል።

ምሥረታው የዘገየውን የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደርን ለመመሥረት እንዲቻል ሀወሓት ባለፈው ሳምንት አቶ ጌታቸው ረዳን በፕሬዝዳንትነት መሰየሙ የሚታወስ ሲሆን፣ የጊዜያዊ መንግሥቱን አወቃቀር፣ በክልሉ በጀት እና በእስረኞች ዙሪያ ከፌደራሉ መንግሥት ጋር ንግግር እየተደረገ መሆኑን ደብረጽዮን አመልክተዋል።

source: BBC Ethiopia

Check Also

ለኢትዮ 360 ተመልከቾችና ደጋፊዎች በሙሉ የቀረበ ጥሪ !!

ለኢትዮ 360 ተመልከቾችና ደጋፊዎች በሙሉ የቀረበ ጥሪ !! ********************************************** #ሼር እናድርግ #እናዛምት ከቅዳሜ ግንቦት 5/2015 …

ቤተክርስቲያኒቱ ከባለፈው የበለጠ ብርቱ ፈተና እየመጣባት ነው። መሳይ መኮነን

ቤተክርስቲያኒቱ ከባለፈው የበለጠ ብርቱ ፈተና እየመጣባት ነው። እነአብይ አሁን ብቻቸውን አይደሉም። ከእነጌታቸው ረዳ ጋር ተጣምረው …

Multi threaded Redundant Dedicated Server in USA and in Europe.